Site icon ETHIO12.COM

እንዲወጡ የታዘዙት የተመድ ሠራተኞች ከአገር መውጣታቸው ተረጋገጠ

– አምባሳደር ታዬ በሌሎች እንዲተኩ ተመድን ጠይቀዋል

በኢትዮጵያ መንግሥት ከአር እንዲወጡ የታዘዙት ሰባቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ከአገር መውጣታቸው ተገለጸ። የተመድ የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) የኮምዩኒኬሽን ባለሙያ ሃያት አቡ-ሳሌህ ሰባቱ ሠራተኞች ከአገር መውጣታቸውን ለቢቢሲ አዋል።

ሃያት አቡ-ሳሌህ ሰባቱ የተመድ ሠራተኞች መቼ እና በምን ሁኔታ ከአገር እንደወጡ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት በአገር ውስጣ ጉዳዮች ጣልቃ ገብተዋል ያላቸውን በኢትዮጵያ የድርጅቱ ውስጥ የሚሰሩ ሰባት የሥራ ኃላፊዎች በ72 ሰዓታት አገር ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበረ ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰባቱ የተመድ ሠተኞች ከአገር እንዲወጡ ያዘዘበትን ምክንያት በገለጸበት መግለጫ ላይ፤ ሠራተኞቹ የአገሪቱን ሉአላዊነትን የሚጥስና ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሚሆኑ ድርጊቶችን ፈጽመዋል ብሎ ነበር።

መንግሥት በዚሁ መግለጫው ከሠራዊቱ ጋር ጦርነት ውስጥ ላሉት የህወሓት ኃይሎች የሰብአዊ እርዳታና የግንኙነት መሳሪያዎች እንዲደርስ ድጋፍ አድርገዋል ብሏል።

በተጨማሪም “ስምምነት የተደረሰባቸውን የደኅንነት አሰራሮችን” መጣስና ለእርዳታ አቅርቦት ተሰማርተው ሳይመለሱ የቀሩ ከ400 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎች “ህወሓት ለወታደራዊ እንቅስቃሴዎቹ እየተገለገለባቸው ናቸው” በማለት እንዲመለሱ ለማድረግ አስፈላጊውን ጥረት አላደረጉም በማለት ቅሬታ አቅርቧል።

መንግሥት በ72 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ካዘዛቸው የተመድ ሠራተኞች መካከል የተመድ የሕጻናት አድን ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አደል ኾደር እና የተመድ የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ማርሲ ቪጎዳ ይገኙበታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተባባሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት ሠራተኞች በሌሎች እንዲተኩ ተመድን ጠይቀዋል።

አምባሳደር ታዬ በትዊተር ገጻቸው ላይ፤ የሰብዓዊ እርዳታ በማቅረብ ሥራ ላይ ያለንን ትብብር ለማስቀጠል ተመድ ከአገር እንዲወጡ የታዘዙ ሠራተኞችን በአስቸኳይ እንዲተካ እንደጠይቃለን ብለዋል።

አምባሳደር ታዬ ጨምረውም አዲስ የሚተኩ ሠራተኞች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ከተመድ ድርጅቶች ጋር በትብብር እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።

Exit mobile version