ኤርዶዋን የአስር አገር አምባሳደሮች “ተቀባይነት” እንዲነሳ አዘዙ

ቱርክ ውስጥ የሚገኙት የአሜሪካ፣ የካናዳ፣ የፈረንሳይ፣ የፊንላንድ፣ የዴንማርክ፣ የጀርመን፣ የኔዘርላንድስ፣ የኒው ዚላንድ፣ የኖርዌይ እና የስዊውዲን ኤምባሲዎች ሲሆኑ ከመካከላቸው ሰባቱ በኔቶ ውስጥ የቱርክ አጋሮች ናቸው። ፕሬዚዳንቱ “ምን መደረግ እንዳለበት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴራችን አስፈላጊውን ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ። እነዚህ 10 አምባሳደሮች በአንድ ላይ በአገሪቱ ውስጥ ተቀባይነት የሌላቸው [ፐርሶና ነን ግራታ] ሊባሉ ይገባል። በአስቸኳይም መፍትሄ ይደረግለታል”


ቢቢሲ አማርኛ – የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይፕ ኤርዶዋን የአሜሪካን እና የፈረንሳይን ጨምሮ የ10 አገራት አምባሳደሮች በአገሪቱ ውስጥ ተቀባይነት የሌላቸው መልዕክተኞች እንዲባሉ ማዘዛቸውን አስታወቁ።

አስሩ አምባሳደሮች ላይ ይህ ውሳኔ የተላለፈባቸው ኦስማን ካቫላ የተባለው ቱርካዊ አክቲቪስት ከእስር እንዲለቀቅ የሚጠይቅ መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

ግለሰቡ ከተቃውሞና ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጋር በተያያዘ ለአራት ዓመታት ጥፋተኛ ሳይባል በአስር ላይ ይገኛል።

ዲፕሎማቶች በተላኩበት አገር ውስጥ ተቀባይነት የሌላቸው [ፐርሶና ነን ግራታ] ተብለው ከተሰየሙ የዲፕሎማቲክ መብቶቻቸው ተነስቶ ከአገር እንዲወጡ ይደረጋል ወይም የመልዕክተኝነት ዕውቅናቸው ይገፈፋል።

በዚህ ሳምንት ታሳሪው አክቲቪስት ካቫላን የተመለከተው መግለጫን ያወጡት ቱርክ ውስጥ የሚገኙት የአሜሪካ፣ የካናዳ፣ የፈረንሳይ፣ የፊንላንድ፣ የዴንማርክ፣ የጀርመን፣ የኔዘርላንድስ፣ የኒው ዚላንድ፣ የኖርዌይ እና የስዊውዲን ኤምባሲዎች ሲሆኑ ከመካከላቸው ሰባቱ በኔቶ ውስጥ የቱርክ አጋሮች ናቸው።

የአውሮፓ ዋነኛ ሰብአዊ መብት ጉዳዮች ተከታታይ አካል የሆነው የአውሮፓ ምክር ቤት፣ ቱርክ የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት የአክቲቪስቱ ካቫላ ጉዳይ በፍርድ ቤት አስኪታይ ድረስ እንድትለቅ የሳተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ እንድታደርግ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷታል።

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ኤስኪሴሃይር በተባለ ስፍራ ቅዳሜ ዕለት ለተሰበሰቡ ሰዎች ባደረጉት ንግግር ላይ አምባሳደሮቹ “ወደ ቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመሄድ ትዕዛዝ ለመስጠት ሊደፍሩ አይገባም” ብለዋል።

ጨምረውም “ምን መደረግ እንዳለበት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴራችን አስፈላጊውን ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ። እነዚህ 10 አምባሳደሮች በአንድ ላይ በአገሪቱ ውስጥ ተቀባይነት የሌላቸው [ፐርሶና ነን ግራታ] ሊባሉ ይገባል። በአስቸኳይም መፍትሄ ይደረግለታል” ብለዋል። ቢሆንም ግን አምባሳደሮቹ ምን ሊገጥማቸው እንደሚችል አስካሁን ግልጽ አይደለም።

ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን የአገራቱ መልዕክተኞች ቱርክን ሊገነዘቧት ወይም ለቀዋት ሊወጡ ይገባል ሲሉ መናገራቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የፕሬዝዳንቱን ንግግር ተከትሎ አስካሁን ድረስ ከአምባሳደሮቹ ምንም የተሰማ ምላሽ ባይኖርም፤ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እርምጃው በሚመለከታቸው አገራት መካከል “ጠንካራ ምክክር” እየተካሄደ መሆኑን አመልክቷል።

እርምጃውን በተመለከተ ይፋዊ መግለጫ ከቱርክ ባለሥልጣናት በኩል አስካሁን አልተሰጠም።

የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሮይተርስ እንዳለው የአገሪቱ አምባሳደር “ከአገር አስከ መባረር የሚያደርስ የፈጸሙት ነገር የለም” ብሏል።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአክቲቪስቱ ጉዳይ ላይ ባወጡት “ኃላፊነት የጎደለው” ባለው መግለጫ ላይ ተቃውሞውን ለመግለጽ አማባሳደሮቹን ማክሰኞ ዕለት ጠርቶ አነጋግሯቸው ነበር።

የአምባሳደሮቹ መግለጫ በአክቲቪስቱ የፍርድ ሂደት ላይ የታየውን “የተራዘመ መጓተት” በመተቸት ይህም “በቱርክ የፍትህ ሥርዓት ውስጥ በሚኖረው የዴሞክራሲ መከበር፣ የሕግ የበላይነት እና ግልጽነት ላይ ጥላውን ያጠላበታል” ብለዋል።

መግለጫው ጨምሮም ጉዳዩ በፍጥነት እንዲቋጭና ቱርክ ግለሰቡን “በአስቸኳይ እንደትለቅ” ጥሪ አቅርቧል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት አክቲቪስቱ ካቫላ ከሰባት ዓመት በፊት ከተካሄደው አገር አቀፍ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ከቀረበበት ክስ ነጻ ቢባልም፣ በኤርዶዋን መንግሥት ላይ ከተሞከረው ወታደራዊ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጋር የተያያዘ አዲስ ክስ ተመስርቶበት በአስር ላይ ይገኛል።

Leave a Reply