Site icon ETHIO12.COM

ሶማሊያና ኬንያ በሚወዛገቡበት የባሕር ይዞታ ላይ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ

ኬንያና ሶማሊያን ሲያወዛግብ በቆየው የባሕር ላይ ይዞታ ይገባኛል ጉዳይ ላይ ኔዘርላንድስ ዘ ሔግ የተሰየመው ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ።

በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ነው የተባለውን አወዛጋቢ የውቅያኖስ ላይ ግዛትን ሁለቱ አገራት እንዲካፈሉት ጉዳዩን የተመለከቱት ፍርድ ቤት አስር ለአራት በሆነ ድምጽ ውሳኔ ሰጥቷል።

የባሕር ላይ ይዞታውን በተመለከተ ኬንያ በትይዩ ያለውን ድንበር ከሶማሊያ ጋር ከስምምነት ላይ መድረሷን ያቀረበችውን መከራከሪያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።

በተጨማሪም በውቅያኖስ ክልሉ ውስጥ ኬንያ የነዳጅ ፍለጋና ቁፋሮ ተግባርን በማከናወን ዓለም አቀፍ ሕጎችን ጥሳለች በማለት ሶማሊያ ያቀረበችውን ክስ ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረግ የካሳ ጥያቄዋን ሳይቀበለው ቀርቷል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር የሚገኘው ይህ ፍርድ ቤት የባሕር ጠረፍ ውዝግቡን በተመለከተ የሰጠው ውሳኔ በአብዛኛው የሶማሊያን ፍላጎት የሚያሟላ መሆኑ ተገልጿል።

ቀደም ሲል ኬንያ ዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት በወገንተኝነት በመክሰስ የሚሰጠውን ውሳኔ እንደማትቀበለው አሳውቃ ነበር።

ሁለቱ አገራት በይገባኛል የሚወዛገቡበት በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ያለው 100,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን የውሃ አካል ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ አለበት ተብሎ ይታሰባል።

ይህ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የሚገኝ የባሕር ላይ ይዞታ ይገባኛል በሚል የተቀሰቀሰው ውዝግብ በኬንያና በሶማሊያ መካከል ላለው የዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት ዋነኛ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።

በአሁኔ ጊዜ የኬንያ የባሕር ጠረፍ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ወደጎን በስተምሥራቅ በቀጥታ ተሰምሮ ሰፊ ቦታን የያዘ ሲሆን ይህም እንዲከበርላት ስትጠይቅ ቆይታለች።

ነገር ግን ሶማሊያ በበኩሏ ከኬንያ ጋር የሚያዋስናት የባሕር ጠረፏ የየብስ ላይ ድንበሯን ተከትሎ ቁልቁል በስተደረቡብ ምሥራቅ እንዲሰመር በፍርድ ቤቱ ተከራክራለች።

አስራ አራት ዳኞችን ያያዘው ጉዳዩን የተመለከተው ቡድን ዘ ሄግ ላይ በሰጠው ውሳኔ ሶማሊያ ቀደም ሲል አሁን ባለው የድንበር ይዞታ ላይ ተስማምታለች በማለት ኬንያ ላቀረበችው ክርክር ማረጋገጫ አላቀረበችም ብሏል።

ዳኞቹ ሁለቱ አገራት በይገባኛል ሲወዛገቡበት የቆየውን የውቅያኖስ ይዞታ ለሁለት የሚያካፍል መስምር በማስመር ውሳኔ አሳልፈዋል።

ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ያለውን ሥልጣን ያልተቀበለችው ኬንያ ውሳኔውን ተፈጻሚ የምታደርገው አይመስልም። ፍርድ ቤቱም ብይኑን ተግባራዊ የሚያደርግበት አቅም የለውም።

ሁለቱ አገራት ያላቸውን የድንብር አለመግባባት በድርድር ለመፍታት ከ11 ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግሥታት የተደገፈ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ነበር።

ነገር ግን ከአምስት ዓመታት ድርድር በኋላ መግባባት ላይ አልተደረሰም በሚል ሶማሊያ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ወስዳዋለች።

ሮይተርስ እንደዘገበው እአአ በ2012 ሁለት ዓለም አቀፍ ተቋማት በአወዛጋቢው አካባቢ የነዳጅ አሰሳ እንዲያካሂዱ ፈቃድ በመስጠቷ ሶማሊያ ቁጣዋን ገልጻ ነበር።

ብይን ከመሰጠቱ በፊት አስተያየታቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት የሶማሊያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማህዲ ሞሐመድ ጉሌድ አገራቸው “በደንብ ላይ በተመሰረተ ሥርዓት ላይ . . . እምነት ስላላት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት አምጥታዋለች” ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት በአገራት መካከል አለመግባባት ሲከሰት የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካል እንደሆነ ይታመናል።

ኬንያ ከዓመታት በፊት ከሶማሊያ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ አሳሪ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ውስጥ መግባት የለበትም በሚል ስትከራከር ብትቆይም ሳይሳካላት ቀርቷል።

ባለፈው ዓመት ኬንያ በፍርድ ሂደቱ ላይ ሳትሳተፍ ቀርታ የነበረ ሲሆን፣ ጉዳዩን ከሚመለከቱት ዳኞች መካከል አንዱ የሆኑት ሶማሊያዊ እራሳቸውን እንዲያገሉ በመጠየቅ ተቃውሞ አቅርባለች።

ባለፈው ሳምንት የኬንያ መንግሥት ጉዳዩ እየታየበት ያለውን ሁኔታ “እንከን ያለበት የሕግ ሂደት” ሲል ተችቶት ነበር።

ጨምሮም በሂደቱ ውስጥ “መሠረታዊ ወገንተኝነት” እንዳለ በመግለጽ ፍርድ ቤቱ አለመግባባቱን ለመፍታት ተገቢው መንገድ አይደለም ብሏል።

Read the original story on BBC Amharic

Exit mobile version