ETHIO12.COM

የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት አገራት ዘርፈ ብዙ የትብብር ግንኙቶችን መፍጠር አለባቸው

ጠንካራና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት አገራት ዘርፈ ብዙ በይነ መንግስታት የትብብር ግንኙነቶችን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት ጥሪ አቀረቡ።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት፤ ጠንካራና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት አገራት ዘርፈ ብዙ በይነ መንግስታት የትብብር ግንኙነቶችን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል።

ሕብረቱ የዘርፈ ብዙ ትብብር ስትራቴጂ ቀርጾ ገቢራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም አገራት እርስ በርስ እና ከልማት አጋር ተቋማት ጋር ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል።

የአገራት የባለብዙ ዘርፍ በይነ መንግስታት ትብብር የምንፈልጋትን ጠንካራና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

አፍሪካ አሁናዊ መልከ ብዙ ፈተናዎች እንደገጠማት ጠቅሰው ለአብነትም ኮቪድ 19 ወረርሽኝና ድርቅን ጨምሮ ሌሎች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችን አንስተዋል።

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ድርጅት እና አባል አገራት ወረርሽኙን ለመግታተ የሰጡትን ምላሽም አድንቀዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ጠንካራ እንዲሆን ተቋማዊ ማሻሻያ እየተደረገ መሆነን ገልጸው፤ የህብረቱ የፋይናንስ ስርዓት ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አስተዳደር እንዲሆን ማስቻል ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፍ ሉቱንዱላ ስብሰባው በአሁናዊ የአፍሪካ ፈተናዎች ላይ ይመክራል ብለዋል።

ሕብረቱ የጀመረው የሪፎርም ስራ ጠንካራ እና አንድነቷ የተጠበቀ አህጉር ለመገንባት ብሎም አፍሪካ በዓለም መድረክ ጎልታ እንድትወጣ የሚያስችል እንደሚሆን ተናግረዋል።

”በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ውስጥ ብንሆንም በተገቢው ጥንቃቄ ስብሰባው በአካል እንዲደረግ ኢትዮጵያ ላደረገችው አስተዋጽኦም አመስግነዋል።

39ኛው የሕብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በቻድ መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በአገሪቷ ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ እንዲዛወር መደረጉ ይታወቃል። ጥቅምት 4/2014 (ኢዜአ)

Exit mobile version