ከዜጎቻቸው ለአስር በመቶ ያህሉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት የሰጡ የአፍሪካ አገራት 15 ናቸው

ከአፍሪካ አገራት መካከል ለ10 በመቶ ዜጎቻቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት የሰጡት 15ቱ ብቻ እንደሆኑ የአፍሪካ ሕብረት አስታወቀ።

ሕብረቱ የኮቪድ-19 ክትባት አቅርቦት ፈተና እንደሆነበት ገልጿል።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የሕብረቱ የጤና የሠብዓዊ ጉዳዮችና የማህበራዊ ልማት ኮሚሽነር አሚራ ኤል ፋዲል በተለያዩ ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

አፍሪካን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከገጠሟት ፈተናዎች መካከል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዋነኛነት እንደሚጠቀስ ኮሚሽነር አሚራ ገልጸዋል።

የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር /አፍሪካ ሲዲሲ/ እና የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት ወረርሽኙን ለመከላከል ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል።

በሽታውን ለመከላከል የኮቪድ-19 ክትባት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዓለም አቀፍ የክትባት ድጋፍ ሲጪ ጥምረት /ኮቫክስ/ አማካኝነት የአፍሪካና ሌሎች በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ክትባቱን እያገኙ እንደሆነ ተናግረዋል።

እ.አ.አ በ2021 በኮቫክስ አማካኝነት የአፍሪካ አገራት 270 ሚሊዮን ክትባት ማግኘታቸውን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

የአፍሪካ ሕብረትም እ.አ.አ በ2021 የአፍሪካ አገራት 10 በመቶ ዜጎቻቸውን መከተብ አለባቸው የሚል ዕቅድ ይዞ ነበር።

ይሁንና እስካሁን ዕቅዱን ያሳኩ አገራት 15 ብቻ እንደሆኑ ኮሚሽነር አሚራ አመልክተዋል።

ደቡብ አፍሪካ፣ ሲሼልስ፣ ሞሪሺየስ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ፣ ኬፕቨርዴ፣ ኮሞሮስ፣ እስትዋኒ፣ ሌሴቶ፣ ዚምባቡዌ፣ ሞሪታኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ቦትስዋና እና ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ ለ10 በመቶ ዜጎቻቸው የኮቪድ-19 ክትባት የሰጡ ናቸው።

ሌሎች አገራት በታሰበው መልኩ ዜጎቻቸውን መከተብ ያልቻሉት በኮቫክስ ጥምረት በኩል ያለው የክትባት አቅርቦት በሚፈለገው መጠን ተደራሽ ባለመሆኑ እንደሆነ ኮሚሽነሯ አመልክተዋል።

የተፈጠረውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት የአፍሪካ ሕብረት ግብረ ኃይል በማቋቋም እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የክትባት እጥረቱን ለማቃለል የአፍሪካ አገራት ከክትባት አምራቾች ጋር ፈቃድ ወስደው የሚያመርቱበት ሁኔታ እንዲመቻች ጥረት እየተረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ አልጄሪያና ግብጽ ከአምራቾች ጋር ውል በማሰር ፈቃድ ወስደው ክትባት ለማምረት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይ ሌሎች አገራት ፈቃድ ወስደው ክትባቱን ለማምረት ፍላጎት እንዳሳዩ የገለጹት ኮሚሽነር አሚራ በዘላቂነት አገራቱ ክትባት የማምረት አቅማቸውን መገንባት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።

የበለጸጉ አገራትም በኮቫክስ ጥምረት አማካኝነት ቃል የገቡትን የክትባት ድጋፍ ተደራሽ በማድረግ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ኮሚሽነር አሚራ በአፍሪካ የሠብዓዊ ድጋፍ ስራዎችን የሚያስተባብር የአፍሪካ የሠብዓዊ ጉዳይ ኤጀንሲ ለማቋቋም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በአፍሪካ እስካሁን የተከተቡ ዜጎች ምጣኔ 17 በመቶ እንደሆነ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ የሚያሳይ ሲሆን እ.አ.አ እስከ 2021 ማብቂያ ድረስ የክትባት ምጣኔውን ወደ 40 በመቶ ለማሳደግ ዕቅድ መያዙን ድርጅቱ ገልጿል።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ማምሻውን ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል

(ኢዜአ)

Leave a Reply