Site icon ETHIO12.COM

በኦሮሚያ ለሚገደሉ ዜጎች የፖለቲካ ቁማርና የሴራ ትንተና ፋይዳ የለውም!!

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ” ሰበር ዜና” ብር ሆኗል። ሃፍረት፣ ሃዘን፣ መራራት ቀርቶ ” ምስጢሩ ይፋ ሆነ፣ መጋረጃው ተገለጠ፣ ሰበር ዜና እንደውረደና ጥብቅ መረጃ… ” እየተባለ ሳንቲም መልቀም ቅድሚያ የተሰጠው ተግባር ሆኗል። የፕሪስ ነጻነት ባፍጢሙ ቢደፋስ ብለን እስክንመኝ ፕሬሱ በአብዛኛው ሕዝብና አገርን ሳይሆን ኪሱን መሰረት አድርጎ እየሰራ ነው። እንደ አገር ያሳፍራል። መውጪያው መንገዱም ግራ ነው። ይህ ሲባል ጨዋና ተቆርቋሪዎች የሉም ማለት አይደለም።

ራሳቸውን ” አክቲቪስት” የሚሉ ቀንና ሌት ሲሳደቡ፣ መርዝ ሲረጩ፣ ሲያተራምሱ፣ ልዩነትና ክፋት ሲግቱ፣ ቃላትና ሃረግ እየሰነጠቁ በድርሰት ሲያነበንቡ የሚውሉበትና የሚያድሩበት መከረኛ የዩቲዩብ መንደር የእለት ጉርሳቸው፣ ከዛም በላይ ለተሸጡበት ዓላማቸው ቅድሚያ የሚሰጡበት እንጂ አገርና ሕዝብን ከችግር የሚታደጉበት አውድ አይደለም። መልካም አሳቢዎችን አይመለከትም።

ሕጻን ሲገደል ” ሰበር መረጃ”፣ እናት ስትሞት ” ትኩስ ዜና፣ ሕዝብ ሲታረድ ” ልዩ ዜና” … ወዘተ በሚልና ይህንኑ ጉዳይ ቀንድና ጭራ እየተከሉለት ሲተነትኑ ውለው የሚያድሩ፣ በመካከሉ ” እናመሰግናለን ለሱፐር ቻት ድጋፍዎ” በሚል ልመናቸውን የሚያካሂዱ፣ በችግሩ ላይ ነዳጅ እየጨመሩ አገሪቱን እያሟሟት ነው።

የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለመወጣት የእርስ በርስ ጭፍጭፍን የሚጋብዙን የኢትዮጵያን የእንግዴ ልጆች የሚደጉሙ፣ የሚደግፉ፣ የሚያበረታቱ፣ የሚያሞካሹ ክፍሎች ለየትኛዋ አገርና ሕዝብ እየሰሩ እንደሆነ አለመረዳታቸው የኢትዮጵያን ሃዘን ድርብ ያደርገዋል። እጅግ የሚያሳዝንና ወራዳነትም ነው። ቀን ቤተክርስቲያን ማታ አክቲቪዝምን እያቀላቀሉ እሳት የሚተፉ ደደቦችን ቁጭ ብለው የሚያዳምጡ ዜጎች ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ መቶኛ ባይሞሉም፣ ከማን ምን መማርና ማወቅ እንደሚፈልጉ ማሰብ ያደክማል።

“እኔ በሃይልና በቁጣ ስናገር ልጆቼ እየሰሙ ተጨነቁብኝ” ብሎ ለራሱ ልጆች የድምጽ ብክለት የሚያስብ ለማኝ፣ አገር ለማፍረስና ሕዝብ እንዲበተን ምድር ቤት ተከራይቶ ማታ ማታ መርዝ እንደሚረጭ ስንቶቻቸን እናውቅ ይሆን? ኢትዮጵያን የማድማቱና የመፈረካከሱ ዘመቻ አገር አልባ እንደሚያደርገን እንዴት መረዳት አቃተን፣ እኛ መደንቆራችንና እነሱን መስማታችን ቢያሳዝንም ይህ እንዲሆን ሌት ተቀን የሚተጉ ዓላማቸው ሲሳካ ምን እንደሚያተርፉ ማሰብ ደግሞ ከሰውነት ደረጃ የሚያወርድ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ በጀት በተመደበለት የትርምስ አጀንዳና አተራማሾች አማካይነት ላለፉት ሶስት ዓመታት ነፍራለች። ከዛ በፊት ለሶስት ዓመታት ለውጥ አርግዛ ስትለበለብ ነበር። በድምሩ ስድስት ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያ ታማለች። በስተመጨረሻ በትግራይና በአማራ ክልል፣ እንዲሁም በአፋር የከፋ ቀውስ ገጥሟታል። በጥቂት ስግብግቦች አማካይነት እየሆነ ያለው ሁሉ እንደ ዜጋ አንገት የሚያስደፋ፣ የሚያሳፍር፣ የሚያሳዝንና የሚጨንቅ ሆኖ ሳለ በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ የፖለቲካና የኪስ ትርፍ ላይ የተጠመዱ ዜጎችን መመለከት ህመሙ ….

ይህን ከላይ ያለውን ያነሳነው በኪራሙ ወረዳ ሀሮ ቀበሌ ባለፉት ተከታታይ ቀናት በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፣ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ተፈናቅለውም ተሰደዋል የሚለውን ሪፖርት መስማታችንን ተከትሎ ነው። ጥቃቱ የሚፈጸመው ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር ግንባር መፍጠሩን ባስታወቀው ኦነግ ሸኔ አማካይነት እንደሆነ የመሰከሩት በህይወት ያሉ የሰለባው ቤሰቦችና የዓይን እማኞች ናቸው። ይህን እውነት መከራከር ወይም አለማመን አይቻልም።

እነዚህ ሰላማዊ ያልታጠቁ ዜጎች ንብረታቸው ተዘርፎ ወደ ኪረሙ፣ ጊዳና፣ ነቀምት መሰደዳቸው ታውቋል። ይህ ቀን እየጠበቀ የሚፈጸምና ምክንያት ሊቀርብለት የማይችል ጭፍጨፋ ማስቆም አልተቻለም። በአማራ ስም የሚነግዱ “አክቲቪስት ነን” ባዮች ተቀርጾ የተላከላቸውን የመጨረሻ ማተራመሻ ቪዲዮ እየተቀባበሉ ተጨማሪ ጥፋት እየጋበዙ ነው።

ሸኔ የሚባለው ቡድን ኦሮሞን እንደማይወክል፣”ተከፋይ ቅጥረ ነፍሰ ገዳይ” መሆኑንን፣ በገንዘብ እየተዋዋለ በክፍያ ጭፍጨፋ እንደሚፈጽም፣ ዓላማና ግብ የሌለው የትህነግ አገልጋይ እንደሆነ በቅርብ የሚያውቁት እያጋለጡ ነው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንትም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሆን ብለው ግድያውን እንደሚያከናውኑት በማስመሰል የሚራባው የፈጠራ ትንተና የምስኪኑን አማራ ስቃይ ያበዛው ካልሆነ በቀር የሚፈይደው አንዳችም ጉዳይ እንደሌለ መረዳት አስፈላጊ ይሆናል።

አንድ ቦታ አንድ ድርጊት ሲፈጸም በቅጽበት ቪዲዮ ተቀርጾ የሚላክላቸው አካላት፣ አንድ ፖሊስ ሰው ሲገል ራሱን ቀርጾ ለምን እንደሚልክላቸው፣ ቤት ሲያቃጥል ራሱን ቪዲዮና ፎቶ አንስቶ ምን እንዲደረግ እንደሚልክላቸው በቅጡ መረዳት ወይም መጠየቅ አግባብ ይሆናል። አለያ ዝም ብሎ የቀረበን ሁሉ መዋጥ ትርፉ ጉዳት ብቻ ነው።

በእርግጥ ይህ ግድያ መደጋገሙና በቁጥጥር ስር ሊውል አለመቻሉ በጉልህ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል። የአካባቢው አስተዳደር ወይም የክልሉ መንግስት ሰፊ ቁጥር ያለው ልዩ ሃይል አሰማርቶ ወይም ነዋሪዎችን አስታጥቆ ራሳቸውን እንዲጠብቁ የማያደርግበት ምክንያት አስቸኳይ ምላሽ ያሸዋል።

የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው “ሸኔ” ከህወሓት ጋር አንድ መሆኑን ካወጀ ለኃላ የብሄር ግጭት ለማስነሳት የተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት እየፈፀመ ነው ሲሉ ተናግረዋል። “ሸኔ” ባለፉት ሶስት ቀናትም ኪረሙ ወረዳ ላይ ጥቃት መፈፀሙንና ንፁሃን መገደላቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪ ከሌላ አካባቢ የመጣ ሳይሆን ፤ በዛው አካባቢ የሚንቀሳቀስ የ “ሸኔ” ተፃራሪ “ፅንፈኛ” ቡድን አለ ያሉ ሲሆን የሚሰራው ድርጊት ከ “ሸኔ” ጋር እንደሚመሳሰል፣ አብሮ የሚኖረውን ማህበረሰብ ለይቶ በማጥቃት የፖለቲካ አጀንዳ ለማግኘት የሚንቀሳቀስ የ “ሽፍታ” ቡድን መሆኑንን አመልክተዋል። ለኢቲቪ በሰጡት ቃል ደግሞ ይህ የ “የሸፍታ” ቡድን የአማርኛ ተናጋሪ ሃይል እንዳለው ገልፀዋል። ይህ አዲስ መረጃ አደገኛና ሊጤን የሚገባው ነው።

“ሁለቱ አካላት ናቸው በንፁሃን ላይ ጥቃት ያደረሱት” የሚሉት አቶ ኃይሉ፣ ከሰሞኑ በነበረው ጥቃት 15 ሰዎች መገደላቸውን ይፋ አድርገዋል፤ ድርጊቱ የተፈጸመው የብሄር ግጭት ለመቀስቀስ ታስቦ እንደነበር ተናግረዋል። እዚህ ላይ አማርኛ ተናጋሪዎቹ እነማን ናቸው? እዛው አካባቢ የሚኖሩ ሰፋሪዎች፣ ወይስ እዛው አካባቢ የሚኖሩ የሌላ ብሄር አባላት፣ ወይስ አማርኛ አቀላጥፈው የሚናገሩ … ልብ ያለው አክቲቪስት ይን መርምሮ ያጋልታል። ክቀጥረኛነትና ከኪስ ማደለብ የዘለለ እምነት ያለው መረጃ አስተላላፊ እነዚህን ክፍሎች መርመሮ ይደርስባቸዋል እንጂ ቁጭ ብሎ ሲሳደብና ተጨማሪ ሽብር ሲያመርት ውሎ አያመሽም።

” የሰሞኑን ጥቃት ማንነት መሰረት አድርጎ ተፈፀመ የሚለውም ሊስተካከል ይገባል ” ሲሉም የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ ኃይሉ አዱኛ ገልጸዋል። ይህ ያልጠራ መረጃ ስጋት የሚያዳብር ሲሆን፣ እስካሁን ባለው መረጃ በተመሳሳይ አካባቢ ሰፊ ቁጥር ያላቸው የሌላ ብሄር ሰፋሪዎች ጥቃት ሲደርስባቸው አለመሰማቱ፣ ቀደም ሲል በመንደር ተደራጅተው በደንብ የታጠቁ መሆናቸው ከስጋት ነጻ እንዳደረጋቸው ያስታወቁት ክፍሎች ሌሎችም ሳይውል ሳያድር ሊታጠቁና ራሳቸውን መከላከል እንዲችሉ ሊደረግ እንደሚገባና በአገር ደረጃ አቅጣጫ ተቀምጦ በአስቸኳይ ወደ ተግባር እንዲገባ አመላክተዋል። ጉዳዩ ያለው እዚህ ላይ ነው። ግፊቱና ጫናውም ሊጠብቅ የሚገባው እዚሁ ነጥብ ላይ ነው። ሌሎች ሰፋሪዎች ተደራጅተው ከታጠቁ ለምን አማራ ተደራጅቶ ራሱን እንዲጠብቅ አይታጠቅም?

መንግስት እያንዳንዱን ቀበሌና መንደር መጠበቅ ስለማይቻለው፣ ህዝቡን አደራጅቶ የራሳቸው ዋስትና ራሳቸው እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባው በተደጋጋሚ መገለጹና የኦሮሚያ ክልልም ወደዚህ አማራጭ እንደሚሄድ ከወር በፊት ማስታወቁ አይዘነጋም። ግን መቼ? ክልሉ ራሱንም አካባብውንም፣ የታች አመራሩንም ሊመረምር ይገባል።

Exit mobile version