Site icon ETHIO12.COM

ክተት ያለው ሕዝብ ሸጥና ጉድባ እየዘጋ ነው፤ መከላከያ መጨረሻው ተቃርቧል አለ

እኔ ሙስሊም አማራ ነኝ! ነፃነቴን በባረነት የማልቀይር አዛውንትም ነኝ፤ ባርነትን አላውቀውም፣ አያቶቼም አያውቁትም፣ በባርነት ከማልፍ ከነ ነፃነቴ ብወድቅ ለእኔ ክብሬ ነው። ግፍን የምሸከምበት ትካሻ የለኝም” ብለው “ተከተለኝ ” የሚል ጥሪ ያቀረቡት የድሬ ሮቃው ጀግና ሀሰን ከረሙ ናቸው። ልክ እንደ እሳቸው ሁሉ ለህልውና ዘመቻው ክተት ያሉ ዋጋ እየከፈሉ በደማቸው ታሪክ እየጻፉ ነው።

የአገር መከላከያ በደቡብ ወሎ ግንባር ሕዝብ ከመከላከያ፣ ልዩ ሃይልና ፋኖ ጋር ሆኖ እየተበተነ ያለውን ሃይ ጥሻ ለጥሻ እየገባና መተላለፊያ እየዘጋ እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል። መከላከያ በኦፊሳል የማህበራዊ ገጹ የሚከተለውን አስፍሯል።

በደቡብ ወሎ ቦሩ ሥላሴ አካባቢ ለጥፋት ተሰልፎ የመጣው ጠላት በመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይል፣ በሚሊሻውና በፋኖው ጥምረት ተመቷል።ከመሳህል ወደ ማርዬ እየተመታ እየሸሸ ያለውን ታጣቂ የአካባቢው ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ከሠራዊቱ ጋር በመሆን ሸጦችንና ጉድባዎችን እየዘጋ ወራሪውን መግቢያና መውጫ እንዳያገኝ እያደረገው ይገኛል።

በሐይቅ አካበቢ የመጣውም ተመትቶ ወደ ሱሉሌ እና ወደ ባሶ ሚሌ አቅጣጫ የፈረጠጠ ሲሆን ከተለያዩ ቦታዎች የመጣው ህዝብ ከሠራዊቱ ጋር ተቀናጅቶ ጁንታውን እግር በእግር እየተከታተለ በደረሰበት እርምጃ እየወሰደበት ይገኛል።

በቆንዲ አካባቢ ወደ ኩታ በር እየመጣ የነበረው የጁንታው ኃይልም በወገን ጦር ተመትቶ አብዛኛው ሙትና ቁስለኛ ሆኗል።ሠራዊቱ ከሕዝቡ ጋር እያደረገው ያለው የተቀናጀ ትግል ለድሉ መገኘት ዋናው ምክንያት ነው ። ትናንት በጋሸና በኩል የመጣው ጠላትም በሠራዊታችን ክንድ ተደቁሶ የሞተው ሞቶ የተረፈው ለመሸሽ እየሞከረ ነው።አሁን ጁንታው ያለ የሌለ ኃይሉ እየተመታበት በመሆኑ የመጨረሻውን የመጠባበቂያ ኃይል እየተጠቀመ ነው።

የማሠልጠኛ፣ የመሣሪያና እና የመገናኛ ማዕከላቱ በአየር በመመታታቸው የጁንታው ሠራዊት ከፊትና ከኋላ ድንጋጤ ውስጥ ገብቷል። በአሁኑ ሰዓት ከተለያዩ አካባቢዎች የዘመቱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከመከላከያ፣ ከልዩ ኃይሉ፣ ከሚሊሻውና ከፋኖ ጋር በመሆን የጀመሩትን ተጋድሎ ማጠናከር ተገቢ ነው። ሕዝቡም በሐሰተኛ መረጃዎች ከመወናበድ ይልቅ ድጋፉንና ትግሉን ማጠናከር ይገባዋል።

Exit mobile version