Site icon ETHIO12.COM

ደመቀ መኮንን ዛሬ ያነጋገሯቸውን የአውሮፓ አገራት ዲፕሎማቶችን ወቀሱ

“የአውሮፓ ህብረት እና አባል አገራት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ የሰብአዊ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።

አቶ ደመቀ ዛሬ በኢትዮጵያ ከፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ሃንጋሪ፣ ኢጣሊያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ፖርቱጋል፣ ሮማኒያ፣ ስዊድን እና ስሎቫኪያ አምባሳደሮች በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ገለጻ አድርገዋል።

ገለጻውም በዋነኝነት በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታና የሰብዓዊ ድጋፍ ላይ ያተኮረ ሲሆን በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ያሉት አንዳንድ አገራት የኢትዮጵያ ወቅታ ጉዳይን በመገንዘብ ለኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ያደረጉትን የሁለትዮሽ ድጋፍ እና ግንዛቤ አድንቀዋል።

አቶ ደመቀ የኢትዮጵያን እውነታዎች ለአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እና ለአባል አገራት ለማሳወቅ ጥረት ቢደረግም እውነታውን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለመረዳት ዳተኝነት መታየቱን በውይይታቸው ወቅት አስርድተዋል፡፡

በአውሮፓ ህብረት እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔን እውቅና ያለመስጠት ፍላጎት አሳይተዋል ሲሉም ወቅሰዋል፡፡ ይህም አሸባሪው የህወሃት ቡድን አጋጣሚውን በመጠቀም በሚያካሂደው የሽብር ድርጊት የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይደረስ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል። በተለይም በአፋርና አማራ ክልሎች በሚገኙ ንጽሃን ላይ አሰቃቂ ግድያና የሰበአዊ ወንጅል እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተቃራኒው የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሰብአዊ ዕርዳታ ባልተገደበ መልኩ ተደራሽ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየሰራ ቢሆንም በህወሃት አሸባሪ ቡድን እየተደናቀፈ ይገኛል ብለዋል፡፡

በዚህም አሸባሪው የህወሃት ቡድን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘትና የኢትዮጵያ መንግስት ስም ለማጠልሽት በማሰብ የሰብአዊ እርዳታው በትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎቻችን እንዳይደረስ እያደረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በዚህ ተግባሩም የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ ሥራዎችን በማደናቀፍ ሕወሓትን ተጠያቂ ማድረግ አለበት ብለዋል።

ሰሞኑን የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ማዕቀብ ለመጣል ያሳለፈው ውሳኔ ሚዛናዊነት የጎደለው እንደሆነም አንስተዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት እና አባል አገራት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ በጦርነቱ ለተጎዱ አማራ እና አፋር ክልሎች የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ጥቅምት 15/2014 (ኢዜአ)

Exit mobile version