Site icon ETHIO12.COM

አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ የምታስወጣ ከሆነ 200 ሺ የሚጠጉ ሴቶች ከሥራ ውጪ ይሆናሉ

አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ የምታስወጣ ከሆነ በፋብሪካዎች ተቀጥረው የሚሠሩ 200 ሺ የሚጠጉ ወጣት ሴቶችና እናቶችን ከሥራ ውጪ ይሆናሉ ሲሉ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ገለጹ፡፡

የምጣኔ ሀብቱ ባለሙያ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት ከሰጠችው ከቀረጥ ነፃ ንግድ ማበረታቻ ዕድል (አጎዋ) ተጠቅመው በአሜሪካ ገበያ ምርታቸውን በሚያቀርቡ ፋብሪካዎች 200 ሺ ያህል ሰዎች የሥራ ዕድል አግኝተዋል፡፡

በእነዚህ ዜጎች ስር ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተዘዋዋሪ የዕለት ጉርሳቸውን ያገኛሉ፡፡ አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ የምታስወጣ ከሆነ በፋብሪካዎቹ ተቀጥረው ከሚሠሩት ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት ወጣት ሴቶችና የልጅ እናቶች ከሥራ ውጪ ይሆናሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከአጎዋን ነፃ የገበያ ዕድል ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ይበልጥ መጠቀም የጀመረች መሆኑን አወስተው፤ አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ የምታስወጣ ከሆነ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መጎዳት ብቻ ሳይሆን ኢንቨስተሮችም ማሽኖቻቸውን ጭነው ወደ ሌሎች የአጎዋ ተጠቃሚ ወደ ሆኑ የአፍሪካ አገራት ሊሰደዱ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡

አሜሪካ በአንድ በኩል በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ ለኢትዮጵያ እሰጣለሁ ትላለች፤ በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ከአጎዋ በማስወጣት በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ አንድ ሚሊዮን አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ከሥራ ውጪ የምታደርግ ከሆነ አመክንዮዊ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ይህንንም ማመዛዘን ያስፈልጋል እያለን የአሜሪካን መንግሥት እየወተወትን ነው ብለዋል።(ኢኘድ)

Exit mobile version