Site icon ETHIO12.COM

በደሴ ከተማ የሚገኙ መረዳጃ እድሮች ለሰራዊቱ ስንቅ አዘጋጁ

በደሴ ከተማ ሆጤ ክፍለ ከተማ ሀገር ግዛት ቀበሌ የሚገኙ 12 የመረዳጃ እድሮች በጋራ በመሆን ለሰራዊቱ ስንቅ አዘጋጁ፡፡

እነዚህ እድሮች ስንቅ ለማዘጋጀት እያንዳንዳቸው 10ሺ ብር ያዋጡ ሲሆን፤ የስንቅ ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ ወደ ሰራዊቱ እንደሚላክ አስተባባሪዎቹ አስታውቀዋል።

ከአስተባባሪዎቹ መሀከል አንዱ የሆኑት አቶ ዘሪሁን ማንደፍሮ ይህ ተግባር የደሴ ህዝብ ለሰራዊቱ አስተማማኝ ደጀን መሆኑን ለማሳየት የተደረገ በው ብለዋል፡፡

12ቱ እድሮች ከ አራት ሺህ 700 በላይ አባላት እንዳላቸው የተናገሩት አስተባባሪው፤ ድጋፋችን ከስንቅ እስከ ግንባር የሚዘልቅ ነው ብለዋል፡፡

የስንቅ ዝግጅቱን እያካሄዱ ያገኘናቸው መምህርት አለም አልአዛር በበኩላቸው “ሀገራችንን ከጠላት ለማዳን ማንኛውውንም ነገር እናደርጋለን” ብለዋል፡፡

እንደ አንድ የደሴ ነዋሪዎች በጠላት ፕሮፓጋንዳ ሳንወናበድ ድጋፋችንን እንሰጣለን ያሉት መምህርቷ “መከላከያ ከጎናችን ነው የሚያሰጋ ነገር የለብንም” በማለት ተናግረዋል፡፡

ከ12ቱ እድሮች የአንዱ ሰብሳቢ እንደሆኑ የሚናገሩት ሼህ እንድሪስ ሀሩን መሀመድ በበኩላቸው “ይህ የተዘጋጀው ስንቅ ሰራዊቱን ያጠግበዋል ብለን አይደለም፡፡ ግን አለንላችሁ ለማለት ነው” ያሉ ሲሆን ሁሉም እድሮች የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ በደስታ ማድረጋቸውን እና ይህም እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version