Site icon ETHIO12.COM

የአሃዱ ሬዲዮ ሰራተኞች”ሐይቅ ሳትያዝ በትህነግ እጅ ገባች”በማለታቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ

የአሃዱ ሬዲዮ ባልደረባ የሆነና በወቅቱ የአርታዒ ስራ ሲሰራ የነበረ የሓይቅ ከተማ ሳትያዝ በትግራይ ነጻ አውጪ ሃይል እጅ እንደገባች አስመስለው በመስራታቸውና በማስተላለፋቸው ፖሊስ አስሮ ፍርድ ቤት እንዳቀረባቸው ተሰማ። የተሳሳተ ሃሰተኛ መረጃ በሬዲዮ ማሰራጨታቸውን አምነዋል።

ባለፈው አርብ በደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ የሚገኘው “ሐይቅ ከተማ በትህነግ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ገብቷል” በሚል ያሰራጨው የአሐዱ ራዲዮ 94.3 የዜና ክፍል ኃላፊ በወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የጀርመን ድምጽ አመልክቷል።

የኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያው ለዘገባው ምንጭ የሆነው የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ለዘጋቢዋ የሰጠው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ዜናው ከተላለፈ በኋላ ከከተማዋ ከንቲባ እና ከነዋሪዎች አረጋግጦ ይቅርታ በመጠየቅ እርምት ወስዶ እንደነበር የጣቢያው ዋና አዘጋጅ ሊድያ አበበ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የመንግስት ሃላፊ የተባሉት ማን እንደሆኑ፣ የት እንደሚሰሩና በምን ሃላፊነት እንደሚገኙ ዘገባው አላብራራም።

ተጠርጣሪዎቹ ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት ቀርበው ለምርመራ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ለምን እንደያዛቸው ለፍርድ ቤት እንዳስረዳው ሁለቱም ጋዜጠኞች ከዜናው መልዕክት ውጪ በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ድርጅት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው መጠርጠሩን እንዳስታወቀ ዘገባው አመልክቷል።

የሬዲዮ ጣቢያው ጠበቃ የኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያው የተሠራው ዘገባ ላይ እርምት መወሰዱ እንዳለ ሆኖ፣ ጉዳዩ በፍትሃብሔር እንጂ በወንጀል የሚያስጠይቅ እንዳልነበር መናገራቸውን ዘገባው ጠቁሟል።

አሃዱ ሬዲዮ በቀጥታ ስርጭቱ የሓይቅ ከተማ መያዟን ሳያጣራ የዘገበው በሃሰተኛ መረጃ ሰዎች በሚፈናቀሉበትና መንግስት የሃሰት መረጃ በመስማት የሚፈላቀሉ ባሉበት እንዲቆዩ መረጃ እየሰጠ ባለበት ወቅት ላይ መሆኑ ታውቋል። የአካባቢው አስተዳደር አካል የሆኑ እንዳሉት ድርጊቱ ተቀነባብሮ የተፈጸመና ሬዲዮውን የሚሰሙትን በሙሉ ለማሸበር ታልሞ የተፈጸመ ስለመሆኑ አመልክተዋል።


YOU MAY LIKE

Exit mobile version