ወዲ ነጮን ጨምሮ በስድሰት የቀድሞ የመከላከያ መኮነኖች ላይ 22 ምስክሮች ቃላቸውን ሰጡ ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት ቀጠሮ ተሰጠ

ሜጀር ጀኔራል ገብረመድህን ፍቃዱ(ወዲ ነጮን) ጨምሮ በስድሰት የቀድሞ የመከላከያ መኮነኖች ላይ 22 የዐቃቤ ህግ ምስክሮች በችሎት ቀርበው ቃላቸውን ሲሰጡ ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት ደግሞ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ ።

ተከሳሾቹ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1)(ሀ)(ለ)፣35 እና 247(ሀ) እና (መ) አንዲሁም የጦር መሳርያ አስተዳደር ቁጥጥር አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀፅ 2/2፣22/3 ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮነኖች ሆነው በተሰጣቸው ኃላፊነት እያገለገሉ እያለ የህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ አባላትና በፌደራል መንግስት ስልጣን ላይ የነበሩ ባለስልጣናት ከፌደራል መንግስት ስልጣን በመነሳታቸው ምክንያት በማኩረፍና በመቀሌ ከተማ በመሸሸግ “የፌደራል መንግስት በአደገኛ አመራሮች እጅ ስለወደቀ የፌደራል መንግስትን በማንኛውም መንገድ በማስወገድ ወደ ስልጣን መመለስ አለብን” በማለት
ለሀገር መከላከያ የታቀደውን የግንኙነት መስመር ላይ የተንኮል ስራ ለመፈፀም በማሰብ ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በፊት ወደ ሰሜን ዕዝ በመጓዝ ዕዙ ውስጥ የሚገኙ የመገናኛ መኮነኖችን ሰብስበውና በየክፈለ ጦሩ እየዞሩ የፕሮግራም ሙሊት እና የሚሞሪ ሲመስ ባትሪ ቅየራ መከወን ካለበት ጊዜ ቀድመው እንዲቀየሩ ትዕዛዝ በመስጠት ፣ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውን የሰሜን ዕዝ የጦር ክፍል ሬዲዮ ግንኙነት ድር እንዲቋረጥ በማድረግ አንደኛው ክፍለ ጦር ከሌላኛው ጋር እንዳይገናኝ በማድረግ ፣ የሰሜን ዕዝ ያልሆነ ሰራዊት መግባቢያ ኮድና ሰነድ በትግረኛ ቋንቋ በማዘጋጀት ለሕውሀት ሰዎች በማደል ፣ ቀደም ሲል የራሳቸውን ሰዎች በከሚቴ በማደራጀት በሀሰት በብልሽት ምክንያት ተወግደዋል የተባሉ የግንኙነት መሳርያዎችን በክልሉ ላደራጁት ህገ ወጥ የታጠቀ ኃይል በማስታጠቅ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በደረሰው ጥቃት በርካታ ቁጥር ያላቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት አንዲሞቱና ከባድ ቁሳዊ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆኑ በፈፀሙት የአገር መከላከያ ሰራዊት መጉዳትና ህጋዊ ፍቃድ የሌለው የጦር መሳርያ ይዞ በመገኘት በቡድንና በተናጥል በፈፀሙት ወንጀል በዐቃቤ ህግ ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል ።

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዐቃቤ ህግ ክስ ከተመሰረተባቸው 21 ተከሳሾች መካከል 4ኛ ተከሳሽ ብርጋዴል ጄነራል ነጋሲ ትኩዕ እና በክስ መዝገቡ ከ8 እስከ 19ኛ ተራ ቁጥር ተከሰው የነበሩ መኮንኖች ጉዳያቸው ወደ ጦር ፍርድ ቤት መዛወሩም የሚታወስ ነው፡፡

ነገር ግን ስድስቱ ማለትም 1ኛ ተከሳሽ የመከላከያ የኮሚኒኬሽንና ኤሌክትሮኒክስ ሳይበር መምሪያ ኃላፊ ሜ/ጀ ገ/መድህን ፍቃዴ( ወዲ ነጮ ) 2ኛ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ሲስተም መምሪያ ኃላፊ ኮ/ል ገ/ህይወት ደስታ 3ኛ የሬዲዮ ግንኙነት መሳሪያ ሬፈራል መሪ ሌ/ኮ ዩሀንስ በቀለ 4ኛ:ብ/ጄ ነጋሲ ትኩዕ 5ኛ ሌ/ኮ ብርሃነ ሊቃኖስ 6ኛ ሻለቃ ብርሀነ ገብሩ 7ኛ ሻለቃ ኃይለስላሴ ግርማይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀርበው የምስክርነት ቃል እየተሰማባቸው ያሉ ተከሳሾች ናቸው ።

በ3ኛው ዙር የዐቃቤ ህግ የምስክር አሰማም ሂደት ከሰኞ የካቲት 28 አስከ ዛሬ መጋቢት 2/2014 ዓ.ም የተሰሙት ምስክሮቹ ከመገናኛ ሬዲዮ መሳሪያ አወጋገድ ጋር ተያይዞ እንዴት ለህውሐት የሽብር ቡድን ተላልፎ እንደተሰጠ ፣ እንዴት የሬዲዮ ግንኙነት ሊቋረጥ ቻለ በሚሉ ጭብጦች ላይና በወንጀል ድርጊቱ የተከሳሾች ተሳትፎና ሚና ምን አንደነበር በመግለጽ የምስክርነት ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል፡፡

ከጥቅምት 17/2014 ዓ.ም ጀምሮ ጀምሮ ባሉት 3 ዙሮች ዐቃቤ ህግ ካስመዘገባቸው 47 ምስክሮች ውስጥ እስካሁን 22 የዐቃቤ ህግ ምስከሮች ቃላቸውን ሰጥተዋል ።

ዐቃቤ ህግም ቀሪ ምስክሮቼ በተለያየ ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተበታትነው ስለሚገኙ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሚኒስቴር ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን ምስክሮችን አንዲያቀርብ ትዕዛዝ አንደሰጥለትና ቀሪ ምስክሮችን ለማሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ እንደሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሚኒስቴር ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን ቀሪ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት ደግሞ ለሚያዚያ 24 /2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።

Via ministry of justice

Leave a Reply