Site icon ETHIO12.COM

 አየር ሃይል ጥቃት አካሄደ “የአየር መከላከያ ኃይላችን እየተዋጋ ነው” ጌታቸው ረዳ

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በትግራይ የመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ሁለተኛው ክፍል ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን የመንግሥት ኮምንኬሽን አገልግሎት ማስታወቁን ተከትሎ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ “የአየር መከላከያ ኃይላችን እየተዋጋ ነው” ሲሉ በቲወተር ገጻቸው አስታውቀዋል።

አየር ሃይል “ትህነግ ወታደራዊ መሣሪያዎችን የሚጠግንበት” ሲል የጠቀሰውን መቀለ የሚገኘውን መስፍን ኢንጂነሪንግ አጥቅቶ በሰላም ወደ ማረፊያው መመለሱ ቢግለጽም፣ አቶ ጌታቸው የድርጅታቸው የአየር መከላከያ ሃይላቸው እየተዋጋ መሆኑን ከማስታወቃቸው ውጪ ስለ ውጤቱ ያሉት ነገር የለም። ገለልተኛ ወገኖች፣ በቀጥታ ከትህነግ መረጃ በማግኘት የሚታውቁ ግለሰቦችም ሆኑ ሚዲያዎ የትህነግ የአየር መከላከያ ሃይሉ ስላስመዘገበው ውጤት እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

አቶ ጌታቸው አያይዘውም ጥቃቱ የተሰነዘረው ሲቪል ነዋሪዎች ላይ እንደሆነ ጠቅሰው ” ያለቀለት / የሞተ መንግስት” የሚወስደው ጥቃት እንደሆነ አመልክተዋል። እሳቸው ይህን ቢሉም የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገለግሎት ” ጎማ ሲተነፍስ በጣም ይጮሃል” በሚል የሰሞኑ ተከታታይ ማስጠንቀቂያና ፕሮፓጋንዳ የሞት ጣር ውጤን መሆኑን አስታውቋል።

ቢቢሲ የአማርኛው ክፍል የትግርኛ አጋሩን ጠቅሶ ” የአይደር ሆስፒታል የአደጋ ጊዜ አገልግሎት አስተባባሪ ነርስ አበበ ሃፍቱ በበሉላቸው ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ህፃናትን ጨምሮ ስድስት ሰዎች በአየር ጥቃቱ ሲገደሉ ከ27 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ተናግረዋል” ሲል ዘግቧል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጥቃቱ ዒላማውን የመታ መሆኑንን ሲያስታውቅ ሰማዊ ዜጎች ስለመጎዳታቸው ያለው ነገር የለም። ይልቁኑም የተሳካ እርምጃ መወሰዱን፣ ጥቃቱም የትህነግን ሎጂስቲክ ማዳከም አካል መሆኑንን ነው ያስታወቀው።

በቅርቡ አቶ ጌታቸው ከመቀለ በራሳቸው ሚዲያ በእንግሊዝኛ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ” ከሰማይ በጣም እርቀው ነው የሚመቱን” ሲሉ በርካቶችን “ያስገረመና ያዝናና ነው” የተባለ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል። የኢትዮጵያ አየር ሃይል የወሰደው ጥቃት ለሰባተኛ ጊዜ ሆኗል።

ዶክተር ደብረጽዮን ከጽሁፍ መግለጫና አቶ ጌታቸው በቲውተር ካሰራጩት በተጨማሪ ባቀረቡት መልዕክት የኢትዮጵያን ሰራዊት ” የአብይ” በሚል ስያሜ ጠርተው እንዳለቀለት በትናንትናው ምሽት ማስታወቃቸው ይታወሳል። ይህ በተባለበት ማግስት የተወሰደው ጥቃት ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ ግን ዝርዝር መረጃ አልወጣም።


Exit mobile version