Site icon ETHIO12.COM

«የትህነግ የሽብር ቡድን ለማጥፋት ሁሉም በየአካባቢው እንዲዘጋጅ»

የፀጥታ ሀይሉ በሚፈጽመው የተቀናጀ ማጥቃት አሸባሪው ቡድን ላይ ድል እየተቀዳጀ ነው:: የትህነግ የሽብር ቡድንን ለማጥፋት ሁሉም በየአካባቢው እንዲዘጋጅ በቀጣይ ትግሉን ለማቀጣጠል አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንም አስረድተዋል።

የጸጥታ ሀይሉ በሚፈጸመው የተቀናጀ ማጥቃት የአሸባሪውን ህወሃት ቡድን እየደመሰሰና ድል እየተቀዳጀ መሆኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሠ ቱሉ እንደገለጹት፤ የፀጥታ ሀይሉ በሚፈጸመው የተቀናጀ ማጥቃት ድል እየተቀዳጀ ነው።

ቡድኑ ባለፋት ጥቂት ቀናት ያለውን ሀይል አሰባስቦ በወረባቦ፤በተሁለደሬ እና በጭፍራ ጥቃት መክፈቱን አስታውሰዋል።

የፀጥታ ሀይሎች በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ “የአሸባሪው ህወሃት አባላት ሙትና ቁስለኛ ሆነዋል” ብለዋል።

አየር ሀይሉ እየወሰደ ባለው እርምጃም በተሳካ መልኩ የአሸባሪው ህወሃት መጠቀሚያዎችን ማውደም መቻሉንም አብራርተዋል።

አሁንም ቡድኑ እኩይ ድርጊቱን የቀጠለ መሆኑን አመልክተው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ከምን ጊዜውም በላይ በአንድነት መነሳት እንዳለበት አብራርተዋል።

“በሁሉም የአገሪቷ አካባቢ መዝመት የሚችል ሁሉ ራሱን ዝግጁ ማድረግ አለበት” ሲሉ የፌዴራል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያን ሊያፈርስ የተነሳውን የትህነግ የሽብር ቡድንን ለማጥፋት ሁሉም በየአካባቢው እንዲዘጋጅ አሳስበዋል።

በቀጣይ ትግሉን ለማቀጣጠል አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንም አስረድተዋል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት ታታሪ ወታደር እና ታታሪ ሠራተኛ እንጂ ታታሪ ወረኛ አይደለም ብለዋል። ሀገሪቱ አሁን የተደቀነባትን የሕልውና አደጋ ለመመከት ከመደበኛ መከላከያ ሠራዊት እና ልዩ ኀይል በተጨማሪ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለትግል ራሱን እንዲያደራጅ ነው ያሳሰቡት።

የተደቀነውን የሕልውና አደጋ ለመመከት የወሎ ወጣቶች እንዳደረጉት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል።

ኅብረተሰቡ ቀየውን ትቶ ከመሸሽ፣ ሰርጎ ገቦችን መከላከል እንዳለበት የተናገሩት ሚኒስትሩ ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው ከተማ የሚደረግ እንቅስቃሴም ሰርጎ ገቡን እና አስተኳሹን ለመለየት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል።

ሚኒስትሩ አሸባሪው ቡድን በሄደበት ሁሉ እንዲቀበር ወጣቱ በርትቶ መሥራት እንደሚጠበቅበት ነው የገለጹት፡፡

ለእርዳታ ወደ ትግራይ የገቡ 860 ተሽከርካሪዎች አለመመለሳቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ ወራሪው እና አሸባሪው ትህነግ እርዳታ ታግዶባችኋል በሚል ማደናገሪያ ሕፃናትን፣ ሴቶችን እና ሽማግሌዎችን በመንጋ ወደ ጦርነት እያሰለፈ መሆኑን ነው ያብራሩት።

ሚኒስትሩ የአማራ እና የአፋር ክልልን በመውረር ዜጎችን ስቃይ ውስጥ የከተተውን ቡድን ለማጥፋት እና በኢትዮጵያ ላይ የደቀነውን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ሀገሩን ለማዳን እንዲነሳ ሀገራዊ ጥሪ መቅረቡን ነው የተናገሩት።

የሽብር ቡድኑ ጦርነቱን እያካሄደ ያለው በኢኮኖሚም ጭምር በመሆኑ አርሶ አደሩ ሰብሉን በመሰብሰብ ለቀጣይ የመስኖ ሥራ ይዘጋጅም ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ እንዲህ ሲሆን ኢትዮጵያን መታደግ እንደሚቻል አስረድተዋል።

Source (አሚኮ) and ENA

Exit mobile version