Site icon ETHIO12.COM

በአዲስ አበባ ከ27ሺህ በላይ ወጣቶች ተደራጅተው ከተማዋን እየጠበቁ ነው

በአዲስ አበባ ከተማ የአሸባሪውን ጸረ ሰላም እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ከ27ሺህ በላይ ወጣቶች ተደራጅተው ከተማዋን እየጠበቁ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የአሸባሪ ሕ.ወ.ሓ.ት ቡድን ኢትዮጵያ ላይ በከፈተው ግልጽ ጦርነት ምክንያት ሰፊ የህዝብ ተሳትፎና አንድነት እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ወቅትም የወጣቱ ሚና የጎላ መሆኑን ጠቁመው፤ የሽብርተኛውን ቡድን ጸረ ሠላም እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በአዲስ አበበ ከተማ የሚገኙ ከ27ሺህ 540 የሚሆኑ ወጣቶች ተደራጅተው አካባቢያቸውን እየጠበቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች “እኔ የከተማዬ የሠላም ዘብ ነኝ ” በሚል መሪ መልዕክት መሠረት ተሰማርተው አካባቢያቸውን ብሎም ከተማቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ ያሉት ቢሮ ኃለፊው፤ ችግሩ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በግንባር ቀደምትነት የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ ሊገታ የሚችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። በአሁን ወቅትም የመከላከያ ሠራዊቱን በመቀላቀልና ለሠራዊቱ ደጀን በመሆን በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሱ እንዳሉ ጠቅሰዋል። ከዚህም ባሻገር አደረጃጀት በመፍጠር ከመሀል ከተማ እስከ መውጫና መግቢያ በሮች ድርስ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን የቁጥጥር ሥራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። 

አቶ አብርሃም እንዳሉት፤ ወጣቶች የራሳቸው መለያ ኖሯቸው በበጎ ፈቃድ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፤ ከህብረተሰብ ተሳትፎ፣ ከሠላምና ጸጥታ እንዲሁም ከፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን ከተማዋ በምትታወቅበት ሠላሟ እንድትቀጥል እየሰሩ ይገኛሉ። በፈረቃ በከተማዋ ውስጥ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር አሰሳ የማድረግ፣ ጸጉረ ልውጦችንና ሰርጎ ገቦችን የማጋለጥ፣ ህገ ወጥ ተግባራትን የመከላከልና የኢኮኖሚ አሻጥሮችን የማጋለጥ ተግባራትን በማከናወን ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ችለዋል። በተጨማሪም ለመከላከያ ሠራዊቱ በሚደረገው የሀብት ማሰባሰብ ሥራ ላይም ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

አቶ አብርሃም “መደበኛው የጸጥታ አካል ሁሉንም አካባቢ ሊሸፍን አይችልም። ቢሸፍን እንኳን በቂ መረጃ ማግኘት የሚችለው ከወጣቱ ነው። ለሥምሪት በቂ ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ የገቡት ወጣቶች እየሰሩ ባለው ተግባር ብዙ ለውጦች ተገኝተዋል” በማለት፤ በተለይ አሸባሪው ቡድን ከተማዋን የሽብር ማእከል ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ቢንቀሳቀስም በወጣቶቹ ጠንካራ አደረጃጀት መክሸፍ እንደቻለ ተናግረዋል። በዚህም በሁሉም መስክ የከተማዋ ወጣቶች ተሳትፎ ውጤታማ ሆኖ መገኘቱን ተናግረው፤ በቀጣይም በሰፊው ሠራዊቱን የሚቀላቀሉና ድጋፍ የሚያደርጉ በርካታ ወጣቶች እንደሚኖሩ ጠቅሰዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን

Exit mobile version