ETHIO12.COM

እዚህ የላስቲክ ቤት ውስጥ ምን ተገኘ? “ሕዝብ ሲተባበር የሚሸሸግ ነገር የለም”

አሁን አሁን ከወንጀል ጋር በተያያዘ ፖሊስ ሕዝብ እንደጠቆመው እየገለጸ ይፋ እያደረገ ያለው መረጃ ከወንጀሉ በላይ እሳቤው አስገራሚ እየሆነ ነው። አንዳንዴ “እንዴት ይህን ሰው አሰበው?” በሚል ” ሰዎች” አስተያየት ሲሰጡ ይሰማል።

እብድ መስሎ፣ ጸበልተኛ መስሎ፣ ቄስ መስሎ፣ በሽተኛ መስሎ፣ ሴት መስሎ … ወንጀል መፈጸሙ እየተገለጸ ይፋ የሚሆኑት መረጃዎች አዲስ አበባ፣ አዲስ አበባ ዙሪያና የክልል ከተሞችን እያዳረሰ ነው። ፖሊስ እንደሚለው ሕዝብ ከውሰነ የማይገለጥ ነገር የለምና በቁጥጥር ስር የሚውሉት ወንጀለኞች ጉዳይ ቁጥር በርክቷል።

የመሳሪያ፣ የሃሺሹ፣ የኮንትሮባንዱ ብዛት እጅ በአናት የሚያስጭን ሆኖ ቢሰነበትም ዛሬ ከዚህ ደሳሳ የላስቲክ ጎዳና ቤት የተገኘው ግን ከግኝቱ በላይ መረጃን ለማሳት የት ድረስ ተርቆ እንደሚኬድ የሚያመላክት ሆኗል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በላስቲክ በተሰራ ቤት ውስጥ በርካታ ሀሰተኛ ሰነዶች እና ማህተሞች መያዛቸውን በምስል አስደግፎ ፖሊስ ይፋ አድርጓል።በአዲስ አበባ ፖሊስ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በክፍለ ከተማው ወረዳ 1 ልዩ ቦታው አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ ግለሰብ ላስቲክ ወጥሮ በሚኖርበት ቤት ውስጥ በተደረገ ብርበራ ነው ሃሰተኛ ሰነዶቹ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት፡፡

ተጠርጣሪው ግለሰብ የሽብር ቡድኖቹን እኩይ አላማ ለማስፈጸም እና ለሰርጎ ገቦች ሽፋን ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በማሰብ እና ህገ- ወጥ ተግባራት እንዲስፋፉ ተባባሪ በመሆን ድርጊቱን በድብቅ ሲፈፅም እንደቆየ ከክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ምክትል ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡የፀጥታ አካላቱ በህዝብ ጥቆማ መነሻነት ባደረጉት ክትትል እና ባከናወኑት ብርበራ ከላስቲክ ቤቱ ውስጥ በርካታ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች፣ ፖስፖርቶች፣ የተለያዩ ክልሎች የቀበሌ መታዎቂያዎች፣ ሌሎች ልዩ ልዩ ሰነዶችና ማህተሞች ተገኝተዋል፡፡

የከተማዋን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላቱ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ያለው ስራ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነና በተለይም በአሁኑ ወቅት የሽብር ቡድኖቹ ለሚያሰራጩት የሀሰት መረጃ ጆሮ ባለመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲል ፖሊስ ጥሪ ማቀረቡን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ብሏል ፖሊስ። ሲጨውርስም “አካባቢዎን ይጠብቁ!ወደ ግንባር ይዝመቱ!መከላከያን ይደግፉ!” ሲል የወቅቱን ጥሪ ከፍ አድርጎ አሰምቷል።

በሌላ ተመሳሳይ ዜና

በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የነዋሪነት መታወቂያን ጨምሮ የተለያዩ ሃሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ የነበረ የወረዳ አስተዳደር ሰራተኛ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት ይገኛል፡፡

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል እና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ዘሪሁን ተፈራ እንደገለፁት አንድ ግለሰብ ሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ ይዞ ሲንቀሳቀስ ህዝብ በሰጠው ጥቆማ በፖሊስ አባላት ተደርሶበት በተደረገ ምርመራ ሃሰተኛ መታወቂያውን ያዘጋጀውን ግለሰብ ማወቅና በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለፃ ሃሰተኛ ሰነዶቹን የሚያዘጋጀው ተጠርጣሪ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባ የስራ መደብ ላይ ይሰራ የነበረ እና በአሁኑ ወቅት በሌላ የስራ መደብ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሃሰተኛ ክብ ማህተም እና ቲተሮችን በማስቀረፅ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ህገ-ወጥ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ ቆይቷል፡፡

ዋና ኢንስፔክተር ዘሪሁን ተፈራ እንዳስረዱት የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ህዳር 04 ቀን 2014 ዓ/ም ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 የረር በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው በተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ባደረገው ብርበራ የተለያዩ ንግድ ፈቃዶች፣ የትምህርት ማስረጃዎች ፣ መሸኛ ደብዳቤዎች፣ የጋብቻ ማስረጃዎች እና ሌሎች ልዩ ልዩ ሰነዶች ተገኝተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ማህተሞች እና ቲተሮች፣ ፍላሾች፣ ላፕቶፕ ኮምፒውተር እና ፎቶግራፍ የተለጠፈባቸውን ጨምሮ ለሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ መስሪያ የሚገለገልባቸው በርካታ ካርዶች እና ሃሰተኛ ሰነድ ሊዘጋጅባቸው የተሰጡ የበርካታ ግለሰቦች ፎቶ ግራፎች በብርበራ ተይዘዋል፡፡

በተጠርጣሪው ላይ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ ዋና ኢንስፔክተር ዘሪሁን አስረድተው የአሸባሪው ህወሃት ቡድን ደጋፊዎች እና ሰርጎ ገቦች የሽብር ቡድኑን ተልዕኮ ለማስፈፀም ማንነታቸውን ቀይረው በከተማችን ለመንቀሳቀስ ሃሰተኛ ሰነዶችን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ በመገንዘብ ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት እየሰጠ የሚገኘው ጥቆማ ለውጤታማ ስራዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡


Exit mobile version