Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ ሚሌ እንዳልደረሰና ኢልዋህና ካሳጊታ ላይ እየተዋጋ መሆኑንን ይፋ አደረገ፤ “ወረኢሉን ለመያዝ የተመመ ሰራዊት ተደመሰሰ፣ አዋጊዎች ተማረኩ”

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ በሚል ስያሜ የሚታወቀው አማጺ ቡድን በድርጅቱ ኦፊሳላዊ የፌስ ቡክ ገጽ ሚሌን እንዳልያዘና፣ ውጊያውን በኢልዋህና ካሳጊታ ላይ እንደሆነ በይፋ አስታውቋል። ቀደም ባሉት ቀናቶች በትግራይ ቲቪ ሚሌ በቁጥጥር ስር መዋሏን አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል። እነ አቶ ጌታቸው ረዳም በቲውተር ይህንኑ ብለው ነበር።

ትህነግ ይህን የገለጸው በጋሸና ፣ ወረኤሉ ፣አጣየና በሚሌ ግምባር ድል ማስመዘገቡን በሰበር ዜና ለወዳጆቹና ደጋፊዎቹ ሲያስታውቅ ነው። በተጠቀሱት ግንባሮች የትህነግ ሃይል ተቆራርጦ ወደሁዋላ እንደማይመለስ ተደርጎ እየተመታ እንደሆነ ቀደም ሲል የአማራ መገናኛ ኤጀንሲ ዘግቦ እንደነበር ይታወሳል። አክሎም በርካታ የዋግ አካባቢዎች እንደተለቀቁ በምስልም አሳይቷል።

“ሰበር የድን ዜና” ሲሎ ትህነግ ይፋ ባደረገው ዝርዝር በተጠቀሱት ግንባሮች “ድንቅ” ድል ማስመዘገቡንና ሰራዊቱ ” ጠላት የሚለውን” የአገር መከላከያ፣ ልዩሃይልና ሚሊሻ እየጠራረገ ወደፊት በመገስገስ ላይ መሆኑንን አመልክቷል።

“ሚሌ ግምባር – በዚሁ ግንባር ጠላት “አለኝ” ብሎ የሚመካበትን ሃይል ሁሉ በማሰለፍ የጀግናው ሰራዊታችንን ጉዞ ለማደናቀፍ በካሳጊታና በኢልዋህ መሽጎ የሞት ሽረት ሙከራዎች ያደረገ ሲሆን፤ ለትግራይ ደህንነት ሲል ማንኛውም ዓይነት ሁሉ የሚከፍለው አይበገሬውና ጀግናው ሰራዊታችን በርካታ የጠላት ሃይልን እየጠራረገና እየበታተነ የጠላትን አከርካሪ ለመስበር ወደፊት በመገስገስ ላይ ይገኛል” ያለው መግለጫው ወደ ሚሌ የሚያደርገውን ጉዞ ስለመቀጠሉ ያለው አነገር የለም።

ከሁለት ቀን በፊት ሚሌ መያዟን ይፋ ያደረገው ትህነግ ዛሬ ጦርነቱ ካሳ ጊታና በኢልዋህ እንደሆነ ያስታወቀው በአፋር ግንባር የስቸኳይ ጊዜ ኮማንደሩ ትህነግ ሚሌን ለመያዝ ሁለት ቀን ያለ የሌለ ሃይሉን ከየግንባሩ አሰባስቦ ከባድ ጦርነት ከፍቶ እንደነበርና በሶስተኛው ሙሉ በሙሉ ተመቶ መመለሱን በይፋ ካስታወቁ በሁዋላ ነው። እንደ ኮማንደሩ ገለጻ ወደ ሚሌ ተጠግቶ የነበረው ሃይል ከተመታ በሁዋላ ወደ ጊታና ኢልውሃ መሸሹን አስታውቀው ጦሩ በህብረት ወደፊት እየገፋ እንደሆነ ካስታወቁ በሁዋላ ነው።

የትህነግ ሃይል በቡርካ በኩል ወደ ሚሌ ለመግባት ከኮምቦልቻ፣ ደሴና ከተለያዩ ግንባሮች ያለውን ሃይል አሰባስቦ በሙሉ ሃይሉ ከፍተኛ ትንቅንቅ ፈጥሮ እንደነበር በመግለጽ አሁን ላይ ተመቶ ከጋሳኪታ ወደ ቡርቃ እየተገፋ ወደ ባቲ ለመግባት መዳረሳቸውን እዛው ግንባር ሆነው አስታውቀዋል። የአፋር ልዩ ሃይል፣ የአማራ ሚሊሻና ልዩ ሃይል፣ መከላከያ የተቀናጀ ጥቃት ማድረጋቸውን አመልክተው በቀሪ ሁለት ቀኖች ወደ ባቲ በመግፋት የሚፈጸም ጉዳይ እንዳለ አመልክተዋል። ይፈጸማል ያሉት ምን እንደሆነ ግን እንዳላብራሩ ትናንት ዘግበን ነበር።

የትህነግ ሰራዊት ለጣፋጭ ድል ወደፊት እየገሰገሰ መሆኑን ያመለከተው መግለጫ “ደህንነታችንና ህልውናችን በፈርጣማው ክንዳችን!ትግራይ ታሸንፋለች! ” ብሎ ይዘጋል። ትህነግ በአራቱም ግንባር በርካታ ከተሞችን መቆጣጠሩና ሰፊ ድል ማስመዝገቡን ሲያስታውቅ ቀድሞ ያደርግ እንደነበረው ምስል ወይም ቪዲዮ አላሰራጨም። ደጋፊዎቹም እንደወትሮ አበባ ሲረጩና የአድናቆት አስተያየት ሲሰጡ አልታየም። ለአፍታ የተደረገችውን ሁሉ ሲዘግቡ የነበሩ የውጭ ሚዲያዎችም ስለተጠቀሰው ድልም ሆነ ስለሌላ ያሉት ነገር የለም።

በወረኢሉ ግንባር ትህነግ ለካቤ፣ ሰኞ ገበያና ወረኢሉ ከተሞችን ተቆጣጥሯል። እንደዚሁም የትግራይ ሰራዊት ከወረኢሉ ወደ ደጎሎ የሚያደርገውን ግስጋሴ ለመግታት በመሸሽ ላይ የነበረውና ሌላ ሃይል ጨምሮ ሙኮራዎች እያደረገ እንደሚገኝና ጀግናው የትግራይ ሰራዊት የተጠቀሰው ሃይልን እየጠራረገ ወደፊት በመቀጠል ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

“ወረኢሉን ለመቆጣጠር አስቦ ኃይሉን ሲያሰባስብ የነበረው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ፣ ፋኖና የአካባቢው ታጣቂ በጋራ በፈጸሙት ጥቃት ተደመሰሰ። በሺዎች የሚቆጠር አሸባሪ የተደመሰሰ ሲሆን ከፍተኛ የአሸባሪው አመራሮችን ጨምሮ በርካቶች ተማርከዋል። አሸባሪው ኀይል በዚህ ግንባር ከሕጻን እስከ ሺማግሌ ያሰለፈ ሲሆን ምርኮኞቹም በየአካባቢው ያለው አሸባሪው ኀይል ተስፋ እየቆረጠ መሆኑን ተናግረዋል። ጀግናዎቹ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ወደ ፊት እየገሠገሡ መሆኑም ታውቋል” ሲል የአማራ መገናኛ ኤጀንሲ ዘግቧል። የተጎዱ ተዋጊፕውችን ምስልም አሳይቷል።


Exit mobile version