Site icon ETHIO12.COM

አሜሪካና አውሮፓን ጨምሮ ከ20 ከተሞች በላይ የተቃውሞ ሰልፍ ይደረጋል – በኮሎራዶ የኢት.ኮ ከሪፐብሊካን ፓርቲ ጋር ዛሬ ይወያያል

በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የውጭ ጫና ዘመቻ የሚያወግዝ የተቃውሞ ሰልፍ በመጪው እሁድ አሜሪካና አውሮፓን ጨምሮ ከ20 በላይ ከተሞች ላይ ሊካሄድ ነው።ትዕይንተ ሕዝቡን በ5 አኅጉራት በሚገኙ 23 ከተሞች ለማካሄድ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ መሆኑን አስተባባሪዎቹ ለዋልታ ገልፀዋል። በዚህም ለኢትዮጵያ የተለየና አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኔትዎርክ ሊቀመንበር ማማይ ወርቁ ከአሜሪካ ከዋልታ ጋር ባደረጉት የቀጥታ የበይነመረብ ቃለመጠይቅ በእለቱ የባይደን አስተዳደር ለሃያ አመታት በአፍጋኒስታን የቆየውን ጦሩን ካስወጣ በኋላ አሜሪካን ለሌላ ጦርነት የሚጋብዝ የውጭ ፖሊሲ ነድፎ የጀመረውን የተሳሳተ እንቅስቃሴ የማውገዝ ተግባር ይከናወናል ብለዋል።ይህን የጦርነት ነጋሪት በአሁኑ ወቅት በተለይ በኢትዮጵያ ላይ እየጎሰመ መሆኑን ለመላው ዓለም የማጋለጥና የመቃወም ስራ ይሰራል ተብሏል።

የባይደን አስተዳደር የሚያሳየውን ጣልቃ ገብነት እና ለአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቆምና የኢትዮጵያን ሉኣላዊነት እንዲያከብር የሚጠይቅ ጠንካራ ጥያቄ እንደሚቀርብም ለማወቅ ተችሏል።ትእይንተ ሕዝቡ ከሚካሄድባቸው ከተሞች መካከል ዴንቨር፣ ካሊፎርንያ፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ደስ ሞይነስ እና ሎዋ ጥቂቶቹ ናቸው።

በአሜሪካ ኮሎራዶ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከሪፐብሊካን ፓርቲ አመራሮች ጋር ዛሬ ውይይት እንደሚያደርግ ገለፀ፡፡በአሜሪካ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኔትዎርክ ሊቀመንበር ማማይ ወርቁ ከዋልታ ጋር በነበራቸው የበይነ መረብ ቆይታ ላለፉት ወራት ከፓርቲው ጋር ውይይት ለማድረግ ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችለው የሪፐብሊካን ፓርቲ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ አለማድረጉን ተከትሎ ጥያቄውን ስለማቅረባቸው ሊቀመንበሯ ጠቁመዋል፡፡የውይይቱ ዋነኛ ዓላማም ጥቅምት 24/2013 ምሽት አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በመከላያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ካደረሰበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ ላይ በከፈተው ጦርነት እስካሁን እየሆነ ያለውን ለፓርቲው አመራሮች ማስረዳት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይ በተለይ ከአሜሪካ የተከፈተባትን ዘመቻና ያልተገባ ጫናን ለማስቆም ፓርቲው ድምጽ እንዲሆንም እንጠይቃለን ብለዋል፡፡

ሊቀመንበሯ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለዴሞክራቶች መመረጥ አበርክቷቸው ከፍ ያለ እንደነበር ጠቅሰው ‹‹የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ከሚያደርገው ያልተገባ ጫና በመነሳት ተክደናል በሚል ስሜትና ቁጭት ውስጥ እንገኛለንም›› ብለዋል፡፡ከዚህ በኋላም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ከጥቅማችን አንጻር እየተደራደርን ድምጻችንን የምንሰጥ ይሆናል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

Exit mobile version