Site icon ETHIO12.COM

“የጥፋት ጥንስስ በሕዝብ ትግል ከሽፏል፤አዲስ አበባ ፍጹም ሰላም ናት”

ይህ የተገለፀው በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋናው መስሪያ ቤት ለጋዜጠኞች በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። መግለጫውን የሰጡት ደግሞ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮምሽነር ሀሰን ነጋሽ ናቸው ፡፡ መግለጫው በርካታ ወቅታዊ፣ ሃገራዊና ከተማዊ ጉዳዮችን የያዘና ያካተተ ሲሆን በተለይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 አፈጻጸም እንዲሁም የፖሊስ የወንጀል ምርመራ ሚናና ተግባራት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በዚህ መሰረት የተቋቋመው የጋራ ግብረኃይል ያከናወናቸው ተግባራትንና ውጤቶችን መግለጫው ዳስሷል ፡፡ እንደማሳያም በሽብር የተጠረጠሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ለህገ-ወጥ ተግባር ማስፈፀሚያ የተጠቀሙበት የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ገንዘቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል። በፍተሻና ብርበራ በርካታ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች ተይዘዋል። በወንጀል የተጠረጠሩ ማንኛውም ቡድኖችና ግለሰቦች በህግ ጥላ ስር ውለዋል፡፡በፖሊስ የሚወስደው እርምጃ በአንድ ብሄር ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሎ ስለሚናፈሰው አሉባልታ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ ሐሰት ነው በማለት አስተባብለዋል፡፡

ወንጀለኛ የተለየ ዘርና ብሄር የለውም።ግለሰቦቹ በማንነታቸው ሳይሆን በተጠረጠሩበት የወንጀል ተግባር ብቻ እየተጠየቁ ነው።ይህንንም የሚከታተል ቡድን ተቋቁሞ አሰራር ተዘርግቶ ክትትል እያደረገ እንደሆነ ገልፀዋል። ምክትል ኮምሸነር ጀነራሉ አያይዘውም ፖሊስ ከዘር፣ ከብሄር ፤ከሀይማኖትና ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ መደበኛ ሰራውን በተገቢው መንገድ እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው ያሉ ግለሰቦችም ሂደቱ በሰብዓዊ ማንነታቸው ላይ ያተኮረ እንዳልሆነና በወንጀል ተጠርጥረው ብቻ እንደሆነም አስረድተዋል ፡፡

ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር ሆኖ በርካታ ውጤታማ የወንጀል ምርመራ ተግባራትን ማከናወኑ ቢታወቅም አንዳንድ የስነ-ምግባር ችግር ያለባቸው ጥቂት የፖሊስ አባላት ግን ጉቦ በመቀበልና የተለያየ ትስስር በመፍጠር ተጠርጣሪዎችን በቂ ምርመራ ሳይደረግባቸው እንዲፈቱ በማድረጋቸው በነርሱ ላይም ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 22 ሰራተኞች ታስረውብኛል 6ቱ ተለቀዋል ለሚባለው ማብራራያ ቢሰጥ? በማለት ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ ምክትል ኮምሽነር ጀነራሉ ሚላሽ ሲሰጡ ማንኛውም የውጭም ይሁን የሀገር ውስጥ ዜጋ በፈፀመው ወንጀል ይጠይቃል፤ወንጀል ሰርቶ ማምለጥ አይችልም ብለዋል።የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል እና ትራፊክ አደጋ ምርምራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ነጋሽ በበኩላቸው አሸባሪው ሕወሓት ግንባር ላይ እያደረሰ ካለው ጥፋት በተጨማሪ በአዲስ አበባ የእኩይ ተግባሩን ሊያሳኩ የሚችሉ የሽብር ተግባራትን ለመፈፀም አቅዶ ሲቀሳቀስ ነበር ብለዋል። ለዚህም እኩይ ተግባሩ ሊያግዙ የሚችሉ ሰዎች እና የጦር መሳርያዎችን በማዘጋጀት ሰፊ ስራ መስራቱን በመግለጫቸው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በህብረተሰቡና በጋራ የፀጥታ ግብረ ሀይሉ ጠንካራ ክትትልና በተካሄዱ ኦፕሬሽን ማክሸፍ ተችሏል ብለዋል።በዚህም ባለፉት 15 ቀናት ውስጥ ብቻ 219 ሽጉጥ፣ 13 ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ተቀጣጣይ ፈንጅዎች ፣41 ክላሽን ኮፍ ጠመንጃ፣ 15 የእጅ ቦንቦች ፣ከ10 ሺሕ 500 በላይ የተለያዩ ጥይቶች፣ 37 የጦሮ ሜዳ መነፅሮች፣ 42 የመገናኛ ሬዲዮኖዎች እና ኮምፓሶችና ለጦርነት የሚያገለግሉና አካባቢን የሚያሳዩ ካርታዎች ከነተጠርጣሪዎቹ ጋር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል። በተጨማሪም ህብረተሰቡ በፖሊስ ላይ እምነት እንዲያጣ ፖሊስ በመምሰል የድለላ ስራ የሚሰሩ ግለሰቦችን ፖሊስ ክትትል በማድረግ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እየተደረገ እንደሆነ ምክትል ኮምሽነሩ ተናግረዋል።

ስለምንድነው አሜሪካ ዜጎቿን ከአዲስ አበባ ቶሎ ውጡ ብላ የምትጨቀጭቀው? ተብሎ ከጋዜጠኞች ለተጠየቀው ጥያቄ ሀላፊዎቹ ሲመልሱ ከአዲስ አበባ ፍፁም ሰላም መሆኗንና ለቀው የወጡት በራሳቸው ጊዜ እንደሚመለሱ እርግጠኛ ነን ብለዋል ሲል ፋና ዘግቧል።

Exit mobile version