Site icon ETHIO12.COM

አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአግዋ ተጠቃሚነት የማስወጣት እንቅስቃሴ ከአሜሪካውያን ባለሀብቶች ትችት ገጠመው

አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአግዋ ተጠቃሚነት የማስወጣት ያልተገባ እንቅስቃሴ ከአሜሪካውያን ባለሀብቶች ትችት እንዳጋጠመው ተገለጸ።

አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ እጇን ለማስገባት ጥረት ማድረግ ከጀመረች የቆየች ቢሆንም ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆማቸው ምክንያት ያሻትን እንዳታደርግ አድርጓታል፡፡

የህዝቡ በጋራ መቆም ያስደነገጣት አሜሪካ የተለያዩ ማዕቀቦችን ከመጣል ጀምሮ ሌሎች በርካታ እጅ የመጠምዘዣ መሳሪያዎቿን ለመጠቀም ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡

ከእነዚህ እጅ መጠምዘዣ መሳሪያዎች መካከልም ኢትዮጵያን ከአግዋ ተጠቃሚነት ማገድ አንዱ ሲሆን ይሀንንም ተግባራዊ ለማድረግ ቀነ ገደብ በማስቀመጥ ለማስፈራራት እየሞከረች ነው፡፡

ይህ የአሜሪካ አስተዳደር ያልተገባ እንቅስቃሴን በተመለከተ በኢትዮጵያ ውስጥ በማምረቻው ዘርፍ የተሳተፉ አሜሪካውያን ባለሀብቶች ጭምር እየተቃወሙት ስለመሆኑም በፎርብስ መጽሄት ላይ የወጣ አንድ ጽሁፍ አስነብቧል፡፡

ጽሁፉ አክሎም አሜሪካ የኢትዮጵያን መንግስት እጅ ለመጠምዘዝ እና ፍላጎቷን ለማሳካት በርካታ ጫና ማሳደሪያ ስልቶችን እየተጠቀመች ስለመሆኑም አትቷል፡፡

መጽሄቱ በሀተታው ላይ እንዳመላከተው አሜሪካ ይህን ውሳኔ የምታሳልፍ ከሆነ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ሲቀረፍ ባለሀብቶቹ ምርቶቻቸውን የተረጋጋ እና አስተማማኝ ወደሆኑ ሀገራት በጥሩ ዋጋ ለመሸጥ የሚገደዱ ሲሆን በዚህም የራሷ የአሜሪካ ገበያ እንዳይረጋጋ ከማድረጉም በላይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን እንደምታስተናግድ ጠቁሟል፡፡

ጽሁፉ አክሎም አሜሪካ እንደ አግዋ ያሉ የንግድ ትብብር ስምምነቶችን ለፖለቲካ መደራደሪያ በመሳሪያነት እየተጠቀመችበት ስለመሆኑም ይጠቅሳል፡፡

አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአግዋ ተጠቃሚነት የምታግድ ከሆነ በቀጥታ ተጎጂ የሚሆኑት በማምረቻው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን እና ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን እንደሆነ ያስታወሰው ጽሁፉ ይህ የአሜሪካ እንቅስቃሴ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነም በቀጣይ በጊኒ፣ በማሊ፣ በማይናማር በካምቦዲያ እና በኒካራጉዋም መሰል ችግሮችን ልትፈጥር እንደምትችል አመላክቷል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ በአሜሪካ ገበያ እንዲያስገቡ የሚፈቅደው አግዋ ስምምነት የተጀመረው እኤአ በ2000 ሲሆን ከ21 ዓመታት በኋላም በመጀመሪያው ዓመት ካስተናገደው የ23 ነጥብ5 ቢሊየን ዶላር የውጭ ገበያ ገቢ ፈቀቅ እንዳላለ ጽሁፉ አስነብቧል፡፡

ይህ ሁሉ የአሜሪካ ያልተገባ ከንግድ ስምምነት የማስወጣት እንቅስቃሴዋ በቀጥታ ከባለሀብቶች ጋር እንድትላተም እንደሚያደርጋት ጠቅሶ በዚህም ባለሀብቶች እና ሀገራት የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈጸም የንግድ ግንኙነታቸውን በተናጠል እንዲያጠናክሩ ሊያስገድዳቸው እንደሚችልም አመላክቷል፡፡

ጽሁፉ ሲያጠቃልልም አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ በትብብር መስራት እንደዋነኛ አማራጭ መከተል እንደሚገባት እና የአግዋ ዕድልን ፖለቲካዊ ጥቅምን ለማስከበር በመሳሪያነት ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባት ጠቁሟል፡፡

ይህ ካልሆነ እና አግዋን ለፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያነት የምትጠቀም ከሆነ ግን ትክክለኛውን የአግዋ አስፈላጊነት፣ ትርጉም እና ምስል ያበላሻል ሲል ጽሁፉ ደምድሟል፡፡

-አካባቢህን ጠብቅ

_ ወደ ግንባር ዝመት

_ መከላከያን ደግፍ

መረጃዎቻችንን ለማግኘት

(ኢዜአ)

Exit mobile version