Site icon ETHIO12.COM

አሸባሪውን ሕወሓት የማዳኑ ዕድል አክትሟል!

ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን ጦርነት ለመቀልበስ የመጨረሻ እርምጃ መውሰድ ጀምራለች:: ለዚህ ደግሞ ከመሪዋ ጀምሮ ወደግንባር በመዝመት ጦርነቱን በድል ለመፈፀም ከጫፍ ደርሳለች:: በተለይ ሰሞኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ወደግንባር መዝመት ተከትሎ መላ ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር በመነቃነቅ የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ ከፍተኛ ትግል እያደረጉ ይገኛል:: በዚህም ከሰሞኑ የተገኙ ድሎች ቡድኑ የመጨረሻ መቀበሪያው ወቅት ላይ መደረሱን አመላካች ዜናዎች እየተሰሙ ነው:: 

ኢትዮጵያውያን በዚህ መልኩ “ሆ” ብለው በአንድነት መነሳታቸውና የሕልውና ጦርነቱን በድል አድራጊነት ለማጠናቀቅ ከጫፍ መድረሳቸው ለመላ ኢትዮጵያውያን ትልቅ የሞራል እና የአሸናፊነት ወኔን የማላበሱን ያህል ከጠላት ወገን ደግሞ ከፍተኛ መረበሽና መደናገጥን መፍጠሩ በግልጽ እየታየ ነው:: በተለይ አሸባሪውን ሕወሓት ከፊት በማሰለፍ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በከፍተኛ ሁኔታ ሲሯሯጡ የነበሩት አሜሪካና ሸሪኮቿ የሰሞኑ የኢትዮጵያውያን አስፈሪ ምት በከፍተኛ ሁኔታ አስደንግጧቸዋል:: በዚህ የተነሳ ይህንን የተነሳ የሕዝብ ማዕበል ለማስቆም ካልሆነም አቅጣጫውን ለማስቀየር ቋጥኝ መፈንቀላቸውንና ጉድጓድ መማሳቸውን በተጠናከረ ኃይል ቀጥለውበታል:: የኢትዮጵያ ጉዳይም ዋነኛ ጉዳያቸው አድርገው እየሰሩበት ይገኛል:: ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ማሳያዎች አሉ:: 

አሜሪካውያኑ ከሰሞኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደሩጫ ለመግባታቸው አንዱ ማሳያ የፕሬዚዳንቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ስለሽብር ቡድኑ የሰጡት መግለጫ ነው:: አምባሳደሩ በመግለጫቸው አሸባሪው ሕወሓት ጠንካራና በማንኛውም ወቅት አዲስ አበባን ለመቆጣጠር የሚችል እንደሆነ ለማሳየት ሞክረዋል:: አምባሳደሩ በዚህ መልዕክታቸው “አሁን ሕወሓት አዲስ አበባ ቢገባ ተቀባይነት የለውም:: ስለዚህ አዲስ አበባ እንዳይገባ ከሕወሓት ጋር ተማምነናል” ሲሉ ሕወሓት አቅም እንዳለው፣ ነገር ግን ወደአዲስ አበባ ከመግባት ያቆመው የነሱ ተማፅኖ እንደሆነ ለማሳየት ሞክረዋል:: እውነታው ግን አምባሳደሩ ይህንን የተናገሩት ቡድኑ በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ውስጥ መግባቱን ስለተረዱና ሕልውናው አደጋ እንደተጋረጠበት ስላውቁ ነው:: 

የአሜሪካ ሴራ በዚህ ብቻ አያበቃም:: አዲስ አበባ ለአደጋ የተጋለጠች ስለሆነ ለቃችሁ ውጡ ከሚለው መልዕክት ጀምሮ ከአዲስ አበባ ለቀው ለሚወጡ ዜጎቻቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጭምር ሲለፈፍ ቆይቷል:: ነገር ግን በሁሉም አቅጣጫ ከአዲስ አበባ በብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች ያሉ አካባቢዎች ሁሉ ሠላም ስለመሆናቸው የውጭ አገር ዜጎች ሁሉ ያረጋገጡት እውነታ ነው:: 

ለዚህ ደግሞ አሜሪካ ዜጎቿን ውጡ ካለች በኋላ አርባምንጭ ደርሰው የተመለሱ የአሜሪካ ዜጎች ጭምር ያረጋገጡት እውነታ ነው:: የአሜሪካ የውሸት ወሬ ፉርሽ አድርጎ ኢትዮጵያ የተገኘው የታዋቂው ላውረንስ ፍሪማን ተግባር የአሜሪካ የውሸት ወሬ ጸሐይ እንደጠለቀበት የሚያመልክት ነው። ከዚህም አልፎ ከአዲስ አበባ ይልቅ ሌሎች አገራት ለአደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ውጡ የሚለውን ዘመቻ ተከትሎ ከአዲስ አበባ ወጥታ ናይሮቢ ላይ የተገደለችው የቢቢሲ ጋዜጠኛ አንድ ማሳያ ልትሆን ትችላለች:: 

ይህ ከኢትዮጵያ ውጡ ዘመቻ አልሳካ ሲላቸው ደግሞ ሌላ መላ መዘየድ ጀመሩ:: በሽብር ስም ብዙ መከራ በማድረስ የሚታወቁት አሜሪካኖቹ በአዲስ አበባ የሽብር ተግባር ሊፈፀም ይችላል የሚል ፕሮፓጋንዳ መንዛት ጀመሩ:: ነገር ግን ሽብርተኝነትን እንዋጋለን የሚሉት እነሱ እንደመሆናቸው ይህ እንዴትና መቼ ሊሆን ይችላል፤ እንዴትስ እንከላከል የሚለውን ሲያነሱ አይታይም:: ምክንያቱም ዋና ዓላማው ሕዝብን ማሸበር ነውና:: ከቦሌ አየር ማረፊያ የሚነሱ በረራዎች ሊመቱ ይችላሉ በሚልም ለማስፈራራት ሞክረዋል:: ይህም አልተሳካም:: 

እነሆ አሜሪካኖቹ ከነዚህ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎቻቸው ሁሉ በስተጀርባ ደግሞ መንግሥትን ለመገልበጥ የሚያስችል ሴራቸውን በጓሮ መጎንጎናቸውን ሰሞኑን የወጡ የዙም ውይይቶች አጋልጠዋል:: በሚስጥር የወጣው ይህ ውይይት በእነ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ፤ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ እና ዶክተር እሌኒ ገብረመድህን የመሳሰሉ የሕወሓት አፍቃሪዎች እንዲሁም አምባሳደር ቲም ክላርክ እና አምባሳደር ያማማቶን የመሳሰሉ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈጻሚዎች የተካሄደ ነው:: 

በሌላም በኩል ለአሜሪካ የሚሰሩ ሌሎች የምዕራባውያን ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶችም ሕወሓት የመጨረሻ እስትንፋሱ እንዳይቆም ሩጫቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል:: ለአብነት በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ጽሑፍ በማቅረብ የሚታወቀው ማርቲን ፕላውት ሰሞኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደግንባር መዝመት ተዓማኒነት ለማሳጣት ጠቅላዩ እንደሚዘምቱ ባሳወቁ አንድ ቀን ልዩነት ውስጥ እስካሁን ድረስ የት ግንባር እንዳሉ ፎቶአቸው አልታየም የሚል ጽሑፍ መለጠፉ ይታወሳል:: ሰሞኑን ደግሞ የፍራንስ 24 ጋዜጠኛ ለፍትሕ ሚኒስትሩ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የት ግንባር ናቸው የሚል አስቂኝ ጥያቄ ሲጠይቁ ተመልክተናል:: 

ከዚህም አልፎ የአሸባሪው ሕወሓት ልሳኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉበትን ለሚጠቁም 11 ሚሊየን ብር እንከፍላለን የሚሉ ቀልዶችን ሲለፈልፉ መሰንበታቸው ጉዳዩ ምን የእግር እሳት እንደሆነባቸው የሚያሳይ ነው:: 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ደሴና ኮምቦልቻ እንዲሁም ቀደም ብሎም በአማራና አፋር አካባቢዎች ገብቶ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ሲያደርስ በዚህ ልክ መተንፈስ ተቸግረው ከቆዩ በኋላ መንግሥት የመጨረሻ እርምጃ መውሰድ ሲጀምር ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም የሚል መግለጫ አውጥተዋል:: ለነሱ ጦርነት ማለት የሽብር ቡድኑ ሲመታ እንጂ እሱ ሠላማዊ ዜጎችን ሲያሸብርና ወደ አዲስ አበባ እየገሰገስኩ ነው እያለ ሲፎከር አይደለም:: ይህ ደግሞ አይን ያወጣ ሚዛን የሳተ የአንድ ወገን ፍርድ ነው:: 

እኛ ኢትዮጵያውያን ውስጣዊ ችግሮቻችንን የመፍታም ሆነ የአገራችንን ሠላም የማስጠበቅ ሙሉ ቁርጠኝነቱና ብቃቱ ስላለን አሜሪካም ሆነች ሌሎች ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳ ያነገባችሁ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ከመንገዳችን ላይ ዞር በሉልን እንላለን:: ምክንያቱም አሁን አሸባሪው ሕወሓት የሚተርፍበት ዕድል አብቅቷልና!

አዲስ ዘመን ኅዳር 21/2014

Exit mobile version