Site icon ETHIO12.COM

ከ300 በላይ የሲቪል ማኅበራት ለአፍሪካ ኅብረት ደብዳቤ ጻፉ

መሰረታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ ከ300 በላይ የሲቪል ማኅበራት ለአፍሪካ ኅብረት ደብዳቤ ጻፉ።

የሲቪል ማኅበራቱ በኢትዮጵያ ኢሕገመንግሥታዊ በሆነ መንገድ የመንግሥት ለውጥን ለማድረግ በሚያሴሩ የተወሰኑ ቡድኖችና ስብስቦች ጉዳይ ነው ግልፅ ደብዳቤውን የጻፉት።

ደብዳቤው ከ300 በላይ በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙ የሲቪል ማኅበራትን በአባልነት በያዘው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በኩል ነው አፍሪካ ኅብረትና ለወቅቱ ሊቀመንበር የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፍሊክስ ቲሽኬዲ የተጻፈው፡፡

ደብዳቤው ሰኔ ላይ የተደረገውን ምርጫ በመጥቀስም የኅብረቱ ታዛቢ ልዑክ ምርጫው ከተወሰኑ የሎጅቲክስና ትግበራዎች ውስንነት ባሻገር ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መካሄዱን ልዑኩ በመግለጫ እንዳረጋገጠም አስታውሷል፡፡

የኅብረቱ መመስረቻ ቻርተር ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ ወይም ከምርጫና ሰላማዊ መንገድ ውጭ በሆነ አግባብ የሚደረግን ሥልጣን የመያዝ አካሄድ አጥብቆ ይቃወማል፤ ከተፈፀመም አገራቱን ከአባልነት እስከማገድ ይደርሳል።

ሆኖም የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን እየሞከረ ቢሆንም ሕገ ወጥ ስብስብና የሽብር ቡድኖች እንዲሁም አንዳንድ የውጭ አገራት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግሥት በኃይል ለማስወገድ ሲሞክሩና ሲያሴሩ ተቃውሞውን የሚገልፅ መግለጫ ለማውጣት አልደፈረም።

ለኅብረቱ የተጻፈው ደብዳቤም አሸባሪው ሕወሓት በኃይል ሥልጣን ለመያዝ እየተዋጋና በዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን የሐሰት ወሬ እየተደገፈ ሲንቀሳቀስ፤ የምዕራባዊያን የአሁንና የቀድሞ ዲፕሎማቶች ከሽብር ቡድኑ ሰዎች ጋር መንግሥትን ስለመገልበጥ ሲያሴሩ አምልጦ የወጣ የምስል ማስረጃ እየታየም ከአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት በኩል ዝምታ መስፈኑን ተቃውሟል፡፡

Walta

Exit mobile version