Site icon ETHIO12.COM

የኢትዮጵያ ጥምር ጦር ወደ ኮምቦልቻ እየገሰገሰ ነው፤ በርካታ የመስመር ከተሞች ነጻ ወጡ

ቀውዝባና ጭላ ከተሞችና አካባቢያቸው፣ አጅባር፣ ተንታ እና ዶባ ከተሞችና አካባቢያቸው፣ ማጀቴን፣ ጭረቲን፣ ከሚሴን፣ ርቄን፣ ወለዲን፣ አልቡኮ ከተሞችን እና የቃሉ ወረዳ አብዛኛው ክፍል ከአሸባሪው ሕወሐት ነጻ ወጥተዋል፡፡በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት፣ በ”ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” ባካሄደው ኦፐሬሽን፣ የተለያዩ ከተሞችን ከአሸባሪው ሕወሐት ነጻ የማውጣቱንና በጥልቀት በመግባት የአሸባሪውን ጀሌዎች የመማረክና የመደምሰስ ተግባሩን ቀጥሏል።

በዚህም መሠረት በጋሸና ግንባር ቀውዝባና ጭላ ከተሞችና አካባቢያቸው ከአሸባሪው ኃይል ነጻ የወጡ ሲሆን፣ በወረኢሉ ግንባር በተደረገው ኦፐሬሽን ደግሞ አጅባር፣ ተንታ እና ዶባ ከተሞችና አካባቢያቸው ነጻ ወጥተዋል። በተያያዘም በከሚሴ ግንባር ማጀቴን፣ ጭረቲን፣ ከሚሴን፣ ርቄን፣ ወለዲን፣ አልቡኮ ከተሞችን እና የቃሉ ወረዳን አብዛኛውን ክፍል በመቆጣጠር፣ ጥምር ጦሩ ወደ ኢንዱስትሪ ከተማዋ ኮምቦልቻ እየገሠገሠ ይገኛል። ዛሬና ትናንት በተደረጉት ከፍተኛ የማጥቃት ኦፐሬሽኖች አብዛኛው የአሸባሪው ኃይል ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲበተን ተደርጓል።

ጥምር ጦሩ በጥልቀት በመግባት የተበተነውን አሸባሪ በመልቀም ላይ ሲሆን አብዛኞቹ ጀሌዎች ሲደመሰሱ ቀሪዎቹ እጅ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በዚህ ኦፐሬሽን አማካኝነት “ተደናብሮ የገባው አሸባሪ ኃይል፣ የዘረፈውን ንብረትና ራሱን ይዞ አይወጣም” ተብሎ የተገባው ቃል በተግባር ተፈጽሟል። አስቀድሞ ነጻ በወጡት በምሥራቅ፣ በምዕራብና በመሐል ግንባር በሚገኙ ከተሞችና አካባቢዎች መንግሥታዊ አስተዳደር ተመልሶ በመደራጀት ሥራውን ጀምሯል።

የአሸባሪው ሕወሐት ጀሌዎች በጠንካራው የወገን ጦር አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተው እየተበተኑና እየተደመሰሱ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ ራሱን በማደራጀት አካባቢውን እንዲጠብቅ፣ ጀሌዎቹን እንዲማርክ፣ እምቢ ያሉትንም እንዲደመስስ፣ የዘረፈውን ንብረትና ትጥቅ እንዳይወጣ እንዲያስቀር መንግሥት ጥሪ ያደርጋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትህዳር 25 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version