Site icon ETHIO12.COM

በከባድ ወንጀልና የመብት ጥሰት የተከሰሱ ጥፋተኛ ተባሉ፤ ድብቅ እስር ቤቶች አዘጋጅተው ያሰቃዩ ነበር

ተከሳሾቹ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ማለትም በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳርና በጎንደር፣ በነቀምቴ፣ በጅማ፣ በሻሸመኔና ቢሾፍቱ፣ በሐዋሳ ከተሞች ውስጥ ድብቅ እስር ቤቶችና መመርመሪያ ክፍሎች እንዲዘጋጁ በማድረግ “የተጠረጠሩ ሰዎችን የመያዝ፣ የማሰርና የመመርመር ሥልጣን ሳይኖራቸው” ሕገ ወጥ ተግባር ፈጽመዋል የሚል ክስ የቀረበባቸውብ ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ።

ቢቢሲ ከችሎት እንደዘገበው በቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተርና በሌሎች የተቋሙ ባለሥልጣናት በቀረበባቸው ክስ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ማሳለፉን አመልክቷል። ክሱን ሲመለከት የነበረው የፈደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን አቶ ጌታቸው አሰፋ እና ምክትላቻውን አቶ ያሬድ ዘሪሁንን ጨምሮ በ26 ተከሳሾች ላይ ነው የጥፋተኝነት ውሳኔ መስጠቱን የቢቢሲ ዘገባ ያስረዳል።

በዚህ የክስ መዝገብ ከተካተቱት ተከሳሾች ዋና ዳይሬክተሩን አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አራት ተከሳሾች ጉዳያቸው እየታየ የቆየው በሌሉበት መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር ገልጿል።

የጥፋተኝነት ብይን የተላላፈባቸው ተከሳሾቹ ከ1984 ዓ. ም ጀምሮ ከሃያ ዓመታት በላይ በአገሪቱ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መሥሪያ ቤት ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች በሚሠሩበት ጊዜ ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጪ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም በሰዎች ላይ ሰቆቃን ፈጽመዋል የሚል ክስ ነው የቀረበባቸው።

በተጨማሪ ከሽብር ወንጀል ጋር በተያያዘ ግለሰቦችን ለወራትና ለዓመታት በድብቅ እስር ቤቶች ውስጥ በማሰር በሚደረግ ምርመራ በዝርዝር የተጠቀሱ ከባድ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ሰቆቃዎችን በመፈጸም ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ሥልጣንን አላግባብ በመገልገል የሚፈፀም ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።

ጉዳዩ ሲመለከት የነበረው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ እንደየተከሰሱበት አንቀፅ ጥፋተኝነታቸው በዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎች የተረጋገጠ በመሆኑ የጥፋተኝነት ውሳኔን ማሳለፉን የፍትሕ ሚኒስቴር ገልጿል።

በዚህም መሠረት ከ26ቱ ተከሳሾች የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አቶ አፅበሃ ግደይ፣ አቶ አሰፋ በላይና አቶ ሽሻይ ልዑል አራት ተከሳሾች በሌሉበት የጥፋተኛ ተብለዋል።

የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁንና ሌሎች ተከሳሾች ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበው ብይኑንን የተከታተሉ ሲሆን ተከሳሾቹ በተሰጠው ብይን መሠረት አንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ተከሳሾቹ ከእስር በዋስ ወጥተው ክሳቸውን እንከታተል ብለው ፍርድ ቤቱን ቢጠይቁም ዐቃቤ ሕግ በዋስትና ጥያቄው ላይ በጽሑፍ አስተያየት ልስጥበት በማለቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ለታኅሣስ 06/2014 ዓ. ም ተሰጥቷል።

ከሦስት ዓመት በፊት ከመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ ቀደም ብሎ የአገሪቱ የደኅንነት መሥሪያ ቤት የሆነው ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ተቋም በተቃዋሚዎች፣ በጋዜጠኞችና በሌሎች ግለሰቦች ላይ ከሕግ ውጪ እስርና ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሲፈጸም እንደቆየ ሲነገር ቆይቷል።

በዚህም ምክንያት በቀድሞው ዋና ዳይሬክተርና በሌሎች ደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ባለሥልጣንት ላይ ክስ ተመስርቶ በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።


MORE NEWS


Exit mobile version