Site icon ETHIO12.COM

“ዶላር እናባዛለን”በሚል ሲያጭበረብሩ የነበሩና የሽብር ቡድን ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

“ዶላር እናባዛለን” በሚል ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሁለት የካሜሮን ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
👉በሀገር ውስጥ ለሚገኙ የአይ ኤስ አይ ኤስ የሽብር ቡድን ታጣቂዎች ሊቀርብ የነበረ የጦር መሳሪያም ተይዟል

በአዲስ አባበ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው አዲሱ ስታዲየም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሀሰተኛ የዶላር ህትመት (ማባዘት) ተግባር ላይ የተሰማሩ ሁለት የካሜሮን ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባደረጉት ጥብቅ ክትትል ግለሰቦቹ እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢፕድ ምንጮች ባደረሱን መረጃ ገልጸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ “ዶላር እናበዛለን” በማለት ከአንድ ግለሰብ 85 ሺህ የኢትዮጵያ ብር በመቀበል ያጠቆሩትን (ያባዙትን) ፎርጅድ ዶላር ለግለሰቡ ለመስጠት በዝግጅት ላይ እያሉ በዛሬው እለት በፀጥታ አካላት እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።

በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ ለሚገኙ የአይ ኤስ አይ ኤስ (ISIS) የሽብር ቡድን ታጣቂዎች የጦር መሳሪያ እና ሎጂስቲክስ በማቅረብ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ባሌ ዞን ደሎመና ወረዳ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በቁጥር ከ10 በላይ የሚሆኑ የሽብር ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጋቸው ይታወቃል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትናንትናው እለት ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባባር በተካሄደ ኦፕሬሽን 6 ክላሽ ከ850 መሰል ጥይት ጋር በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉን ምንጮቻችን አስታውቀዋል።

ይህንን የጦር መሳሪያ እና ሽብርተኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋልም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የተቀናጀ ሥራ ማከናወናቸውን ምንጮቻችን ጨምረው ገልጸዋል።

Exit mobile version