Site icon ETHIO12.COM

እነጃዋር መሀመድ ባቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ ላይ ዐቃቤ ሕግ መልስ ሰጠ

ተከሳሾቹ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ የዕርስ በዕርስ ግጭት በማነሳሳት በወንጀል ህጉ አንቀጽ 240 እና ሽብረተኝነትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ተላልፋችኋል በሚል የወንጀል ክስ የቀረበባቸው መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

ከዚህ በፊት በነበሩ የችሎት ውሎዎች ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ነፃ የሚባሉ ግለሰቦች በአስፈጻሚ አካላት እየታሰሩ በመሆኑ በፍቃዳችን በችሎት አንቀርብም በማለት ለመደበኛው ፍርድ ቤት መግለጻቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ተከሳሾች በሌሉበት ክርክሩ ቀጥሎ ምስክሮቼ ይሰሙልኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቆ የስር ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በሌሉበት ጉዳያቸው ይታይ ሲል ብይን መስጠቱም የሚታወስ ነው፡፡

ይሁንና የጃዋር መሀመድ፣ የበቀለ ገርባ:፣ የደጀኔ ጣፋና የሀምዛ አዳነ ( ቦረና) ጠበቆች የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔን ተገቢነት የለውም ሲሉ ባለ 5 ነጥብ ምክንያቶችን ጠቅሰው ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ አቤቱታቸውን መርምሮ “ያስቀርባል” በማለት በይግባኙ ላይ ዐቃቤ ህግ መልስ እንዲሰጥበት ለታህሳስ 6 /2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።

በዚህም መሰረት ዐቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎትና ለይግባኝ ባይ ጠበቃ 06 ገፅ በጽሁፍ የተዘጋጀ መልሱን አቅርቧል።

ዐቃቤ ህግ በሰጠው መልስ በዋናነት ይግባኝ ባዮች ያቀረቡት ጥያቄ መልስ የማያገኝ ከሆነ ፍርድ ቤት አንቀርብም በሚል ከቀጠሮ የቀሩ ሲሆን ይህም ምክንያት አጥጋቢ ባለመሆኑ የቀረበውን ቅሬታ በተመለከተ የይግባኝ ባዮች የፍርድ ቤት ስልጣንና ነጻነትን የሚጋፋ ከመሆኑም በላይ ህግን መሰረት ባላደረገ ማስረጃ የተደገፈ ነው።

ተከሳሾች ከተከሰሱበት ድንጋጌ አንጻር የወ/መ/ስ/ህ/ቁ 160 እና ሌሎች ድንጋጌዎችን ይግባኝ ባዮች እያወቁ ችሎት ለመቅረብ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው በሌሉበት የክሱ መሰማት ሂደት እንዲቀጥል መወሰኑ ህግን መሰረት ያደረገ ውሳኔ ነው ሲል ዐቃቤ ህግ በመልሱ አብራርቷል፡፡ በዚህም መሰረት ዐቃቤ ህግ ለ2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተከሳሾች አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግ በሰጠው መልስ ላይም ጠይቋል፡፡

ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ተከሳሾች በቀጣይ ፍርድቤት ቀርበው መከራከር ይፈልጋሉ ወይም አይፈልጉም የሚለውን ለመረዳት በጠቦቆቻቸው በኩል ተጠይቀው በይግባኙ ላይ ለመከራከር ለጥር 17/ 2014 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።

በወንድም ሰማህኝ

Exit mobile version