ETHIO12.COM

በሌቦች አገዛዝ (ክሌፕቶክራሲ) ተገዝግዛ፤ ገደል አፋፍ ላይ የቆመችው ሱዳን ገመና

ከጌታቸው ወልዩ (ሜክሲኮ ባህረ-ሰላጤ)

ውድ ወገኖቼ እንደ ምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ጽሑፌ በሱዳን ያለውን እጅግ ጉድ የሚያሰኝ የአገርን አደራ አጭበርብሮ በመብላት በሚታወቀው “ክሌፕቶክራሲ”
(የሌቦች አገዛዝ፤ የሱዳንን ጄነራሎች፣ የደኅንነት ሹሞች፣ የመንግሥታዊው ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ አመራሮች፣ ዘብጥያ የሚገኙት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ሌተና ጄነራል ዑመር ሀሰን አልበሽር ቤተሰቦችና የጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐሜቲ /ሔምዲቲ) የሌቦች አገዛዝ ገመና፤ በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፌ እንደ ሹራብ ክር እተረትረዋለሁና እጅግ አጽንኦት ሰጥታችሁ ትከታተሉት ዘንድ በማክበር እጠይቃለሁ።

ውድ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች፦ አንድ ጎረቤት አገር በቁሟ፤ እንደ ሸንኮራ አገዳ ተመጥጣ ስትተፋ፤ እንደማትፈለግ እቃ ተቆጥራ ከላይ ወደ ታች-ከታች ወደ ላይ፣ ከቀኝ ወደ ግራ-ከግራ ወደ ቀኝ ስትገፋ፤ እንደ ማገዶ እንጨት በስለትና ዱልዱም መጥረቢያ እየተፈለጠች በቁሟ ስትማገድ፤ አሊያ ለጥቂቶች ጥቅም ተብሎ በበረሃ እሳት ስትንቀለቀል ወይም ስትነድ ማየት አያሳዝነም?

የሌቦች አገዛዝ የአገር ሞግዚትና አሳዳሪ ሆኖ፤ የአገዛዙ ቀኝ እጆች አገራቸው ጤናማ የአገር መውደድ ኅሊና ያለው፤ አገርና ሕዝቡን አክባሪ፤ ለነገው መጪው ትውልድ ዛሬ በጎ ሥራ ሠሪ የሆነ ትውልድን እንዳታፈራ፤ ገና ከማለዳው እያወላገዱና እያጣመሙ ሲመሯት ሳይሆን ሲያሽመደምዷት ማየትስ ትሻላችሁ? ለማወቅና ለመጠንቀቅ ብላችሁ “አዎ!” ካላችሁ፤ አንኳር አንኳር መረጃ ከነእፍታ መረቁ ጀባ እነሆ ብያችኋለሁ።

በቅድሚያ ግን፦ ከሙስሊም ወንድማማቾች ኅብረት ጋ ግንኙነት (ዝምድና) ያለውን ብሔራዊ እስላማዊ ግንባርን የተካው መንግሥታዊው ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ (The National Congress Party) በምኅጻረ-ቃል “ኤንሲፒ” አባላት የሆኑ ነጋዴዎች (NCP businessmen)፣ የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት የነበሩት ሌተና ጄነራል ዑመር ሀሰን አልበሽር ቤተሰቦች፣ የሱዳን ሪፑብሊክ የመከላከያ ኀይል የሆነውና አገሬው በአጭር አገላለጽ “ኤስኤኤፍ” እያለ የሚጠራው የሱዳን ጦር ኀይሎች (The Sudanese Armed Forces-SAF) አካል፣ የቀድሞው የሱዳን ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት (The Sudanese National Intelligence and Security Service-NISS) እና በጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐሜቲ /ሔምዲቲ) የሚመራው የተጠባባቂ ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኀይሎች ጦር በአጭር ገለጻ “አርኤስኤፍ” (RSF) በጋራ የአገረ-ሱዳን ምጣኔ ሀብትን (በግልና በቡድን ሀብት አከማቾተው) በበላይነት እንደሚመሩ ምን ያህሎቻችሁ ታውቃላችሁ?

አስቡት እስቲ?! የአገር አውራ ፓርቲ አባላት በፓርቲ ሽፋን ስም ነጋዴዎች ሲሆኑ፤ አገርና ሕዝብን የሚያክል አደራ ተረክቦ የነበረ ፕሬዚዳንት ቤተሰቦች፣ ዘመዶችና ጓደኞች በዝምድና ሙስና (nepotism) ተሳስረው፤ የአገር ሀብት አጋብሰው ዓይን ያወጡ ነጋዴዎች ሲባሉ፤ ለአገር ክብር ከሚሰለፉ የሠራዊት አባላት መካከል በተለይ በርካታ ጄነራል መኮንኖች የአገርና ሕዝብ አደራን ሙልጭ አድርገው በልተው የለየላቸው ነጋዴዎች ሲሰኙ፤ የአገር ምስጢር መጠበቅ የሚገባቸውና የአገርና ሕዝብ አደራን የተቀበሉ የደኅንነት ሹመኞች እልም ያሉ ሞላጫ ነጋዴዎች ተብለው ሲጠሩ፤ አወቃቀሩ ጥያቄ ቢያስነሳም ፈጣን ድጋፍ እንዲሰጥ የተዋቀረ ጦር እንደወረደ በሚባል ደረጃ በፈላጭ ቆራጭ አዛዡ ጄነራል እየተመራ የአገር ሀብት እየመዘበረ በቀላሉ የማይሞላ ካዝናና ከአገር አልፎ የውጭ አገር ካዝናዎችን በዘረፈው የሱዳን ሀብት ሲሞላ “ምርጥ ሀብታም ነጋዴ” እየተባለ ሲንቆለጳጰስ አያሳዝንና አያስቆጭም ትላላችሁ?

በሱዳን ሙያተኞች ማኅበር፣ በሱዳን አብዮታዊ ግንባር፣ በብሔራዊ የስምምነት ኀይሎች፣ በሱዳን ንቅናቄ ኮሚቴዎች፣ በሱዳን ጥሪ (ኮል)፣ በዩኒየኒስት ማኅበር እና በ”ኖ ቱ ኦፕሬሽን ኤጌነስት ዉሜን ኢኒሼቲቭ” የተዋቀረውና በርካታ ሲቪልና የታጠቁ ሽምቅ ኀይሎች ኅብረት በሆነው፤ የነጻነትና ለውጥ ኀይሎች (The Forces of Freedom and Change-FCC)ጥምረት፤ ወይም በነጻነትና ለውጥ ስምምነት (Alliance for Freedom and Change -AFC) የሚታገዘው መንግሥታዊው የፀረ-ሙስና (ንቅዘት) ኮሚቴ እንደጎርጎሮሳውያኑ ቀመር በ2019 እንደገለጸው፤ ከ1 ነጥብ 06 ቢሊዮን ዶላር እስከ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የሚገመት በዘረፋ የተካበተ ሀብት በሱዳን ትልቁ መንግሥታዊው ፓርቲ “ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ” መሪዎች፣ ጓደኞቻቸውና ሽርኮቻቸው (cronies) መዳፍ/ቁጥጥር ሥር ይገኛል።

የዚሁ “የብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ” አመራሮች፤ ብዙ ቢሊየን ዶላር ከአገራቸው ሱዳን (እየዘረፏት አገራቸው ከተባለች) በመመዝበር ወደ የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች፣ ማሌዥያና እንግሊዝ ማሸሻቸውን የሱዳንን ጉዳይን “እህ?!” ብለው እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን ከ2010 አንስቶ ከፍተኛ ምርምር እያደረጉ ያሉት ዶክተር ዢያን ባፕቲስት ጋሎፒ በጥናታቸው አመልክተዋል።

ማን ነበር “የሱዳን ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ መሪዎች ከጓደኞቻቸው (ቢጤዎቻቸው ጋር ቁማር መጫወት ጀመሩ።” ብሎ የተናገረው? (Sudanese NCC leaders went gambling with their cronies.) ጎበዝ! “የፓርቲው መሪዎች፦ የሥራ-አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች፣ የፖሊት ቢሮና የዘርፍ ሥራዎችን ለመገምገም ስብሰባ ጀመሩ!” ይባላል እንጂ እንዴት ቁማር ቤት ሄዱ ይባላል?

የቀድሞው የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ እንደገመቱት፤ የሱዳን የቀድሞ ፕሬዚዳንት አልበሽር በበኩላቸው፤ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አመት በ2010 ዘጠኝ (9) ቢሊየን ዶላር ከሱዳን መዝብረው፤ ወደ እንግሊዝ ባንኮች ሳያሸሹ አልቀሩም። ጉዳዩም በሕግ ባለሙያዎች እየተጣራ ይገኛል። ውድ አንባብያን ወገኖቼ፦ ፍርዱን ለእናንተ ትቸዋለሁ።

በነገራችን ላይ “የነጻነትና ለውጥ ኀይሎች” በምኅጻረ-ቃል “ኤፍኤፍሲ” (FFC)፤ የሱዳን ፕሬዚዳንት የነበሩት ሌተና ጄነራል ዑመር ሀሰን አልበሽርን ከሥልጣን ለመመንገል ይካሄድ የነበረውን ሕዝባዊ አመጽ በበላይነት የመራውና ለሚያዝያ 11 ቀን 2011 ዓመተ ምህረት (ኤፕሪል 19/ 2019) የመንግሥት ለውጥ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ የሲቪልና የታጠቁ ሽምቅ ኀይሎች ኅብረት (ጥምረት) ነው።

ለምሳሌ ጄነራሎችን ከወሰድን፤ አብዛኛዎቹ ሱዳን ጄነራሎች ሱዳንን አሳፍረዋታል (የሀፍረት ማቅ አልብሰዋታል)። በአጭሩ አዋርደዋታል። ሱዳን በጄነራሎቿ ተዋርዳለች። የሱዳን ጄነራሎች ፖለቲካዊ አካሄድ፤ አገር አዋራጅ ፖለቲካን (affront/ affronted politics) የሚያቀነቅንና በተግባርምየሚተረጉም የተሽመደመደና የውርደት ፖለቲካዊ ጉዞ የሚከተል ከሆነ ውሎ አድሯል።

በርካታ የሱዳን ጄነራሎች አዋራጅ ፖለቲካዊ መም ላይ የሚያንደረድሩ፤ ለጊዜያዊ ጥቅምና ሆዳቸው ያደሩ፤ የአገርን ሉዓላዊነትና የዜግነት ክብር ከማረጋግጥ ይልቅ፤ ወደ አንዳንድ ምዕራባውያን፣ በዐረቡዓለም ላሉ የምዕራባውያን ተገዳዳሪዎችና ግብጽን ጨምሮ የምዕራባውያን ምስለኔ ወደ ሆኑ አገሮች የሚያንጋጥጡ፤ ተላላኪና አዋራጅ ፖለቲካዊ ጎዳናን የመረጡ፤ አድርባዮች (opportunists)፣ አስመሳዮች(phoneys)፣ ስግብግቦች (Sudanese gluttonous generals)
፣አጭበርባሪዎች (fraudesters)፣ እምነት የማይጣልባቸው (untrustworthy/untrustworthiness) እና የሌቦች አገዛዝን (rules of thieves) የሚከተሉ ግለኞችና ሙሰኞች ናቸው።

ለዚህም ነው “የሱዳን ጄነራሎች እንኳን ግብራቸው፤ አመለካከታቸው ራሱ ሱዳንን አዋርዷታል” እስከ መባል የደረሰው። (Sudanese generals attitudes/opinions really affronted the Republic of the Sudan.)

እነዚሁ ሁሉ የበርካታ ሱዳናውያን ጄነራሎች መገለጫዎች ወይም ማሳያዎች ጄነራሎቹን በጅምላ ለመውቀስና ክብራቸውን ለመቀነስ፤ አሊያም ለማዋረድና ከከፍተኛ ጄነራልነት ሹመታቸው በከንቱ ለማውረድ በደፈናው የተለጠፈላቸው አይደለም። ይኸውም ጄነራሎቹ ከደኅንነት ሹማምንቱ ጋር በማበር፤ አሊያ በሌብነት የጥቅም ገመድ በመተሳሰር የፈጸሟቸውና እየፈጸሟቸው ያሉ አገር አዋራጅና የአገር ቁመናን አንገዳጋጅ እኩይ ተግባራት እንዲህ በቀላሉ ተጠቅሰው እንደማያበቁ በአሳማኝ ማስረጃ እያጣቀሱ መናገርና መተንተን አይከብድምና።

ለእኩይ ተግባሮቻቸው ማሳያም አያሌ ወፋፍራም የእውነታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። በዚህም መሠረት፦ ቅድሚያ ቅጥል ስማቸውን ብንመለከት:- ጄነራል ሰሊጥ፣ ጄነራል ወርቅ፣ ጄነራል ሥጋ፣ ጄነራል ስንዴ፣ ጄነራል ዱቄት፣ ጄነራል ፕላስቲክ፣ ጄነራል ፔትሮሊየም፣ ጄነራል መሬት፣ ጄነራል እገሌ እያልን “በሕዝባር”(backslash ) አሊይ “እና ወይም” (and/or) በማለት እየለያየን እጅግ በርካታ እኩይነታቸውን መጥቀስ እንችላለን። ለመሆኑ ስለሕዝባር ጄነራሎችስ ምን ያህል (Backslashs generals) ታውቃላችሁ?

እሺ ሌላው ይቅር፤ እንደው የአገር ወርቅ ሀብትን እየሸጠ ለግሉ ሀብት ያጋበሰ፤ የአገሩን ወታደሮች በቅጥረኝነት አሰልፎ ክብራቸውን ሸጦ ብዙ መቶ ሚሊየን ፔትሮ ዶላርን ተቀብሎ እንደ ትራስ የተንተራሰ፤ የአገሩን ባንኮች እንደ ግሉ ታዛዥ ሎሌዎች ከእግሩ መዳፍ ሥር አድርጎ የደቆሰ፤ የጥንት ሦስተኛ/አራተኛ ክፍል ሳይንስ መጽሐፍ ላይ የነበረውን እባብ አይቶ ሸሸ እንደሚባለው ተማሪ፤ ከትምህርት ደጃፍ በሩቁ ቆሞ ባለማወቅ ገመድ ተተብትቦ የተኮፈሰ፤ በብዙ ሺ ንጹሐን ሱዳናውያን ግድያና መቁሰል የሚጠረጠር፤ በሱዳን ፖለቲካዊ እርምጃ ከፊት ሆኖ በዋናነት የሚቆምር ጄነራል አታውቁም? ይህ ጄነራል፦ ሞሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ወይም በሥፋት በሚታወቅበት መጠሪያው “ሐሜቲ /ሔምዲቲ” የሚባለው ጄነራል ነው።

የቀድሞው የጦር አበጋዝ (warlord)፤ ኋላ ላይ የሱዳን ተጠባባቂ ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኀይሎች (Paramilitary Rapid Spport Forces) አዛዥ እና በአሁኑ ወቅት ከሌተና ጄነራል አብዱል ፈታህ አል-ቡርሃን ቀጥሎ የሱዳን ጊዜያዊ ሽግግር ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር የሆነው ሌተና ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳግሎ፤ ከምዕራብ ዳርፉር የጄበል አምር ወርቅ ማዕድን ማውጫን በመቀራመት ወርቅ እያስወጣ በማስቸብቸብ የታወቀ፤ በየመን እርስ በርስ ጦርነት በሳዑዲ ዐረቢያ መራሹ የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች፣ ግብጽና ሌሎች አጋሮቻቸው ጥምር ጦርን ደግፎ ቅጥረኛ ወታደሮችን በመላክ፤ ከተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች ብዙ መቶ ሚሊየን ዶላር የተቀበለ፤ ከቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ሌተና ጄነራል ዑመር ሀሰን አልበሽር ጄነራል መኮንኖች አንዱ ነው።

ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐሜቲ /ሔምዲቲ) እና የሚመራው የተጠባባቂ ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኀይሎች ጦር በምኅጻረ-ቃል “አርኤስኤፍ” (RSF)፤ በሱዳን ካሉ ሰፊ የወርቅ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ጋር ከባድ የሆነ የተጠላለፈ የፋይናንስ መረብና ጥብቅ ትስስር እንዳላቸው፤ የባንክ መረጃዎች/ማስረጃዎችና ሰነዶችን በሱዳንና በተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች ባሉ ባንኮችና ኩባንያዎች በምስጢር እንደሚያስቀምጡ የግሎባል ዊትነስ ኦርግ አንድ ዘገባ አረጋግጧል።

አንዲት ቅንጣት የማጋለጫ ማሳያ ማቅረብ የሚፈለግ ከሆነ፤ የጄነራል ሐሜቲ /ሔምዲቲ) ጦር የሆነው “አርኤስኤፍ” (RSF)፤ በስሙ በተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች አቡ ዳቢ ብሔራዊ ባንክ አሁን “ፈርስት አቡ ዳቢ ባንክ” የሂሳብ ማንቀሳቀሻ አካውንት እንዳለው መጥቀስ ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን ጄነራል ሔምዲቲ ከታናናሽ ወንድሞቹ አንዱ ወንድሙ የሚመራው አጠቃላይ የንግድ ኩባንያ በተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች ውስጥ ይገኛል።

ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐሜቲ /ሔምዲቲ) በወንድሙ አብድልራሂም ዳግሎ በሚመራው አል-ጁነይዲ ኩባንያ አማካይነት፤ እንደ አውሮፓውያኑ ስሌት በ2018፤ ዱባይ ውስጥ በአራት ሳምንታት ውስጥ አንድ ቶን ወርቅ በ30 ሚሊየን ዶላር በመሸጥ በአመት 390 ሚሊየን ዶላር አግኝቷል። እንግዲህ አንዱ “የጄነራል ወርቅ” ጉዳይ እንዲህ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ጄነራል ዳጋሎ (ሐሜቲ /ሔምዲቲ) የሚመራው “አርኤስኤፍ” ዱባይ ላይ ወርቅ ሸጦ ሪል ስቴት ኩባንያ ይከፍታል። ከዚያም ባለፈ ሰሜናዊ ሱዳን ተጉዞ ሁለት መቶ ሺ ኤከርስ (80937.1 ሄክታር/809.3 ካሬ ኪሎ ሜትር) የእርሻ ቦታ ገዝቷል። ውሃው አይታሰብም፤ እድሜ ለዓባይ ወንዝ! እናንተ ደግሞ “ጄነራል ስንዴ” ና “ጄነራል መስኖ/መሬት” እያላችሁ ቁጠሩ።

በሌላ በኩል የወታደራዊ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን (ጄነራል ሥጋ) በበከሉ፦በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት በሰሜን ኑባ ተራሮች በካዳሩ አርባ ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ዘመናዊ የቄራ አገልግሎት መስጫ ኩባንያ አለው። ጎበዝ! ጄነራል ሐሜቲ /ሔምዲቲስ እንዴት ይቅርበት?! እናም ጄነራል ሐሜቲ ሩቅ ሳይሄድ በካርቱም የቄራ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት እያስገነባ ይገኛል። ወይ ጄነራል ዳጋሎ (ሔምዲቲ)? በዚህ ደግሞ “ጄነራል ሥጋ” ሊሰኝ በቅቷል።

እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው፤ ሚያዝያ 3 ቀን 2011 ዓመተ-ምህረት ( እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ቀመር ኤፕሪል 11 ቀን 2019)፤ የአገሪቱ ወታደራዊ ኀይል መፈንቅለ-መንግሥት አካሄዶ የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ሌተና ጄነራል ዑመር ሀሰን አልበሽርን ከሥልጣን ካሰናበተና ዘብጥያ ካወረደ በኋላ፤ በሱዳን የደረሰውን ቀውስ ተከትሎ፤ የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ የከፋ የፋይናንስ መናጋት ገጥሞት የነበረ መሆኑ ነው። አሁንም ቢሆን በከፍተኛ አደጋ ላይ ይገኛል። ታዲያ የሚገርመው ጄነራል ሐሜቲ /ሔምዲቲ)፤ ከአገሩ ሱዳን ወርቅ ማውጫ ከዘረፈው ገንዘብ ውስጥ፤ “የሱዳን ማዕከላዊ ባንክን ለማረጋገት 1,027 ቢሊየን ዶላር ወደ ባንኩ የሂሳብ ማስቀመጫ (አካውንት) አስገብቻለሁ! ነዳጅ፣ ስንዴና መድኃኒት ግዙበት!” ብሎ ትእዛዝ ጭምር የሰጠ እጀ- ረዥም አዛዥና ናዛዥ የጦር ሹመኛ ነው።

ከዚያም በሱዳን ሕዝብ “ይህን ሁሉ ገንዘብ ከየት አመጣኸው? አንተና ‘አርኤስኤፍ’ ገንዘቡን ከየት አመጣችሁት?” ብለው ሲጠይቁት፤ ጄነራል ሐሜቲ /ሔምዲቲ) ወይም “ጄነራል ወርቅ” እንዲህ አለ።
“ለሱዳን የተጠባባቂ ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኀይሎች ጦር-‘አርኤስኤፍ’ (RSF) ተዋጊዎቻችን የምንከፍለው ደሞዝ ከውጪ አገሮች አግኝተናል። ገንዘቡን በየመን እርስበርስ ጦርነት በሳዑዲ መራሹ ሠራዊት ጎን ተዋጊዎቻችን በማሰለፋችን ከጥምር ጦሩ የተበረከተልን ነው። ቀሪውን ገንዘብ ከወርቅ ማምረቻችን ከተገኘ ወርቅ ሽያጭና ተጓዳኝ ዘርፎች አግኝተናል።” ሲል በድፍረት የተናገረ ነው።

እንዲሁም ይኸው ጄነራል በቁጥር አንድ ሺ የሚሆኑ ቶዮታ ፒክአፕ የጭነት ተሽከርካሪ መኪናዎችን ከውጭ አገር አስገዝቶ ወደ ሱዳን ያስገባ፤ ከቅርብ አለቃው ከሌተና ጄነራል አብዱል ፈታህ አል-ቡርሃንና ሌሎች ጄነራሎች ጋር ተባብሮ፤ በበርካቶቹ መኪናዎች ላይ ዲሽቃና ፒኬኤም ከባድ መትረየስ በማስጠመድ፤ የሱዳን ሠራዊት በሌተና ጄነራል አል-ቡርሃን እየተመራ በጭነት መኪናዎቹ ላይ ሆኖ የኢትዮጵያን ጠረፋማ አካባቢዎች እንዲፈታተን መንገድ ያመቻቸ እሳትጫሪ፤ ነገር ጎርጓሪ ጄነራል ነው።

ውድ አንባብያን፦ በጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የለየለት ዓይን ያወጣ፤ ጥርሱን ደጅ ያሰጣ፤ የአገር ሀብት ዝርፊያና የሕዝብና አገር ሀብትን ከአገር የማሸሽ የወረደ ቅሌት ትገረሙ ይሆናል። ነገር ግን በሱዳን የሚገኙ ከ250 የሚልቁ ግዙፍ ኩባንያዎች በተለምዶ “ጥገኛ ኩባንያዎች” (parastatal companies) በአገሪቱ ጄነራሎች እና የመረጃ፣ ስለላና ፀጥታ ሹመኞችን ጨምሮ በደኅንነት ባለሥልጣናት ባለቤትነትና ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙና እነዚህ ሹመኞች በሌቦች አገዛዝ ዘዬ መሠረት “ጥገኛ” የሚሰኙትን ኩባንያዎቹን እንደ እንዝርት እንደሚሽከረከሯቸው ምን ያህሎቻችሁ ሰምታችኋል?

የሚገርማችሁ ነገር የሱዳን ገንዘብ ሚኒስትር ኢብራሒም አል-ባዳዊ አንጀታቸው አርሮና በእልህ ስሜታቸውን ተወጥሮ “በሱዳን ከ250 የሚበልጡ ኩባንያዎች በጄነራሎችና የደኅንነት ሹማምንት በባለቤትነት የሚተዳደሩ በመሆናቸው፤ በየዓመቱ ወደ ሱዳን መንግሥት ግምጃ ቤት መግባት የሚገባው ሁለት ቢሊየን ዶላር ሊታጣ የግድ ብሏል።” በማለት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ቀመር በ2019 ላይ እስከ መናገር ደርሰዋል።

ጎበዝ! “መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል (ይሸጣል)” የተባለው ለዚህ ነው። የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ደግሞ፤ በሱዳን ጄነራሎችና ደኅንነት ባለሥልጣኖች የሚዘወሩት ከ250 የሚበልጡ ኩባንያዎች “የሱዳን ምጣኔ ሀብት ሞተሮች” ተብለው በለበጣ የመንቆለጳጰሳቸው ጉዳይ ነው። ድርጊታቸው በደንብ ከተጤነ ግን “ይሉሽን ባልሰማሽ-ገበያም ባልወጣሽ።” ተብሎ የሚያስተርት ነው።

ለነገሩ ዓለም በበርካታ ክፍሎቿ የምትሰጣቸው ብያኔዎችና ውሳኔዎች ከሕጋዊነትና ፍትሐዊነት የሰማይና የምድር ያህል ሲርቁ ይሰተዋላል። ለአብነት ያህል፦ በረሃብና ጠኔ ተገርፎ ከመደርደሪያ ላይ ከብዙ ዳቦዎች መካከል አንድ ዳቦ ያነሳውን (ሌብነት ከሆነ የሰረቀውን) “ሌባ! ሌባ!” ብላ ስሙን አጥቁራና አስጠፍታ፤ በፖሊስና ፀጥታ ኀይሎች እጁን የፊጥኝ አሳስራ ወህኒ /እስር ቤት (ማረሚያ ቤት አላልኩም) ስትወረውር፤ በሚሊየንና ቢሊየን ዶላሮች የአገርና ሕዝብ ሀብት ዘርፎ ለሹመኞችና
ሕጋዊ ውሳኔ ሰጪዎች ጉርሻ /ምልጃ/እጅ መንሻ/አፍ ማስዘጊያ/ማባበያ የሰጠውን ግለሰብ፤ የአገርና ሕዝብ ሀብት ዘርፎ የከበረውንና ወደ ውጭ አገራት ገንዘብና ሌላ የአገር ሀብት ያሸሸውን፤ ሳትይዝ፣ ሳትከስ፣ ሳትበይንና ሳትወስን፤ ጭራሹኑ “ታዋቂ ባለሃብት፣ ባለጸጋ፣ ቱጃር፣ ኢንቨስተር፣ የንግድ/የቢዝነስ ሰው፣ የልማት አጋር፣ የችግር ጊዜ ደራሽ፣ በጎ አድራጊና አርአያ” የሚሉ የግራሞት የዳቦ ስሞች ሰጥታ፤ ከወርቅ እስከ አልማዝ ቀለበት፣ የደረት ባጅና የአንገት ሀብል አበርክታ፤ የመዋዕለ-ነዋይ ማፍሰሻ መሬት፣ መኖሪያ ቤትና ዘመናዊ መኪና ሽልማት ከባንክ ብድር ጋር አመቻችታ፤ አሞግሳ፣ አወድሳ፣ አስኮፍሳና ካባ አልብሳ፤ ሲያሻት አመስግናና አስመስግና አስቆንና አስጀንና “ጀግና” ብላ ስትጠራ ተስተውሏል። ሱዳንም ይህን ስታደርግ ኖራለች፤ ሌላ ምን አደረገች¿¡

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት፤ ይህ በየዓመቱ ወደ ሱዳን መንግሥት ግምጃ ቤት ከመግባት ይልቅ የሱዳን ጄነራሎችና ደኅንነት ሹሞች ካዝና ውስጥ በየአመቱ የሚገባው ሁለት ቢሊየን ዶላር፤ ሱዳን በገጠማት የዳቦና ነዳጅ እጥረት፤ የሸቀጦች ዋጋ ንረትና ግሽበት የተነሳ ለነዳጅና ስንዴ መደጎሚያ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር 2019 ጀምሮ በየአመቱ ለሴፍቲኔት ከመደበችው ገንዘብ ጋር እኩል ያህል መሆኑ ነው። ሱዳን ከጎርጎሮሳዊያኑ አመት 2019 አንስቶ እስከ 2021 ድረስ ለማኅበራዊ ሴፍቲኔት 6 ቢሊየን ዶላር የመደበች ሲሆን፤ በተመሳሳይ ጄነራሎቹና የደኅንነት ባለሥልጣኖቹ የማይሞላና የማይጠረቃው ጎተራ ውስጥ የገባው ገንዘብ በበኩሉ 6 ቢሊየን ዶላር የሚሆን ነው።

እናስ?! ዜጋ የዳቦና ነዳጅ ያለህ? በሚልበት፤ የሸቀጦች ዋጋ ንረትና ግሽበት ጣሪያ በነካበትና መፈናፈኛ ባሳጣበት ሁኔታ፤ የአገርና ሕዝብ ሀብትን ሰርቆ፤ ከሕዝብ አፍና ጉሮሮ ነጥቆ፤ ሕጋዊና ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ፤ የግል ካዝናንና ጎተራን መሙላት ምን አይነት የጭካኔ ደረጃ (ጫፍ) ላይ መድረስ ነው?

እስቲ ይታያችሁ?! ከከቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ሌተና ጄነራል ዑመር ሀሰን አልበሽር ከሥልጣን መወገድ በኋላ፤ ዘጠኝ ሚሊየን (9) ሕዝብ አስቸኳይ እርዳታ በሚፈልግበት፤ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሕዝብ ቤት አልባ በሆነበት፤ ኮቪድ-19 ከባድ ራስ ምታት በአገሪቱ ከባድ ፈተና በፈጠረበት፤ ከአገሪቱ 44 ሚሊየን ሕዝብ 65 በመቶው በድህነት ወለል ላይ ለመኖር በተገደደበት ፤ በቤተሰብ ዕርዳታ መርሐ-ግብር ሰማንያ በመቶ (80%) ወይም አራት አምስተኛው የሱዳን ሕዝብ በወር አምስት ዶላር ($ 5) ለመስጠት፤ ከታኅሳስ 2012 ጀምሮ ከረጂ ድርጅቶች 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ቃል ተገብቶ አገሪቱ ደጅ በምትጠናበትና በሰቀቀን ላይ ባለችበት ሁኔታ አገርን መስረቅና ማራቆት ምን የሚሉት ግለኝነትና ራስ ወዳድነት ነው?

ውድ አንባብያን የበርካታ ሱዳን ጄነራሎች የአገር ሀብት ዝርፊያና ያለአግባብ ሀብት ማከማቸት ግራ ግብት ያለው አንዱ የዋህ ምን ብሎ ጠየቀ መሰላችሁ? “አረ! ለመሆኑ? የሱዳን ጄነራሎች አገራቸውን የዘረፉት ለምንድን ነው?(Why Sudanese generals robbed their country?) ሌላኛው ደግሞ ምን ብሎ መለሰለት መሰላችሁ!? “መስረቅና መዝረፍ ሥራቸው ስለሆነ!”

እንደው ጎበዝ አጀንዳው የሱዳን ሪፑብሊክ ሆነና የጎረቤት ገመና ስንቱ ይገለጣል በማለት ለጊዜው ተዉኩት እንጂ የደቡብ ሱዳን በርካታ ባለሥልጣናት የአገር ሀብት ዝርፊያ ራሱ እኮ “እግዚኦ!” ያሰኛል።

ለማንኛውም ሱዳንን ልምሻ እንዳጠቃው እግር አጥመልምሎና ጃርት እንደበላው ዱባ በሁሉ አቅጣጫ ቦርቡሮ ለዚህ ሁሉ የነውጥ ማጥና የድህነት አረንቋ ውስጥ ከከተቷት ኡኩይ ተግባራት አንዱ የባለሥልጣኖቿ የሌቦች አገዛዝ በመሆኑ፤ “እገሌ ሲታማ ለእኔ ብለህ ስማ!” ብሎ የሱዳንን እለታዊ እንቅስቃሴ በቅርበት መከታተል የግድና የግድ ይላል።

ከሱዳን ሕዝብ ሦስት አራተኛው በአል ፋሻጋ የድንበር ውዝግብ አፈታትና የኢትዮጵያ ታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ለሱዳን በሚሰጠው ጠቀሜታ ላይ ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚሰለፍ ጥናቶች ያመለክታሉ።

እንዲሁም የሱዳን ሉዓላዊ ሽግግር ምክር ቤት የግብጽ ትሮይ ፈረስ ስለመሆኑና የሱዳን ዘመነኛ ጄነራሎችና አንዳንድ የሲቪል ሹመኞች፤ በውጭ ኀይሎች በተለይም በምዕራባውያንና አፋሽ አጎንባሽ ዐረብ አገሮች የሚገፉና የሚደገፉ ከመሆናቸው አኳያ በእጅ አዙር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እየፈጸሙ ያሉትን ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም በመቃወም የኢትዮጵያ አካሄድን የሚቀበሉ ሱዳናውያን ቁጥር እጅግ በርካታ (ወደ ሰባ አምስት በመቶ ገደማ) ስለሆነ፤ ኢትዮጵያን የሚደግፉ ሱዳናውያንን መተባበር ያስፈልጋል። በሱዳን የሕዝብ አመጽ እየሰፋና እየገፋ በመምጣቱ፤ ለምዕራባውያንና ለምዕራባውያን የወርቅ እንቁላል የሚጥሉ ዶሮዎች አይነት ለሆኑ ዐረብ አገሮች የሚያሸረግድ አሻንጉሊት መንግሥት ወደ ሥልጣን እንዳይመጣ በጥንቃቄ መከታተል የግድ ይላል፤ በማለት ስሰናበታችሁ፤ ዘመናችሁ የስኬትና ድል ይሁን በማለት ነው።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

የኢትዮጵያ አምላክ አገረ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!
አሜን!

Exit mobile version