Site icon ETHIO12.COM

የስብእና ልእልና፤ የሞራል ከፍታ !!!


ከ100 አመት በፊት እንደ ዘመኑ አይን አውጣ ሌቦች አምጣ ብለው ሳይሆን ውሰድ የተባሉትን የ50ሺ ብር ጉቦ የተጠየፉት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተ/ማርያም !!!

ፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ አስጠርተውኝ፣ ሙሴ ሳቡሬ የሸጠልን የመስኮብ ጠመንጃና 40 ሚሊዮን ጥይት ድሬደዋ ስለደረሰ ወደ ድሬደዋ ሄደህ ርክክብ እንድትፈጽም ሲሉ ጠየቁኝ፡፡

ልጅ ኢያሱ ግን ለዚህ ጉዳይ እኔ እንደማላስፈልግ በመግለጽ ሌላ ሰው እንዲሄድ ቢያዙም ከተማርኩባት ሩሲያ የመጡትን
መሳሪያዎች ለመመርመር የኔ መሄድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጬ በማሳመን ወደ ድሬደዋ እንድሄድ ፈቀዱልኝ፡፡

ወደ ድሬደዋ ደርሼ ሆቴል እንዳረፍኩ ማካልዲስ የሚባል የግሪክ ሰው የሙሴ ሳቡሬ ወኪል ነኝ በማለት ወዳረፍኩበት ሆቴል መጣ፡፡ ነገ ጠዋት መሳሪያዎቹን እያወረድን መመርመር እንጀምራለን፣ ጧት ጉምሩክ እንድትመጣ ብዬው ተለያየን፡፡ ይኸው ሰው በድጋሚ ማታ ወዳረፍኩበት ሆቴል በመምጣት ልክ ብዙ ዘመን እንደሚያውቀኝ በወዳጅነት አይነት ያነጋግረኝ ጀመር፡፡

በመጨረሻም ወጪ ይበዛብዎታል በማለት ሙሴ ሳቡሬ 50ሺ ብር እርዳታ ስጥ ብለውኛል በማለት ገንዘቡን ሊሰጠኝ ሞከረ፡፡ በከንቱ አትድከም፣ ምንም አያስፈልግም፣ ይልቅስ ነገ ጥዋት እንድትመጣና ስራችንን እንድንሰራ ብዬ አሰናበትኩት፡፡

በነጋታው በቀጠሯችን መሰረት ለናሙና 1 ሳጥን ጠመንጃና 10 ሳጥን ያህል ጥይቶችን አስከፍቼ መመርመር ጀመርኩ፡፡ ጠመንጆቹ ዝገዋል፣ በብርጭቆ ወረቀት እየተፈገፈጉም ተቀብተዋል፡፡ ጥይቶቹም ተበላሽዋል፣ ቀለሆቹ ተቦርቡረውና ተጎድተው አረሮቹና ቀለሆቹ ተለያይተዋል፣ ባሩዱም ከቀለሆቹ ውስጥ እየተዘረገፈ በስብሶ ነጥቶ ጨው መስሏል፡፡ ይህንኑ ባሩድ በእሳት እያቃጠልኩ ስመረምረው መቃጠል አይችልም፡፡

እንደዚሁ ከየረድፉ አምስት አምስት ሳጥኖች እያስከፈትኩ በየቀኑ ከመረመርኩ በኋላ የምርመራዬን ውጤት ለሳቡሬ ወኪል አሳየሁት፡፡ ለፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊስም ጠመንጆቹ ዝገው የተጠረጉ አሮጌ ጠመንጆች እንጂ አዲስ አለመሆናቸውን፣ ጥይቶቹም ሁሉም የተበላሹና ጥቅም የማይሰጡ መሆናቸውን በመዘርዘር መሳሪያዎቹን እንደማልረከብ በሪኮማንዴ ሪፖርት ጽፌ ላኩላቸው፡፡

የዛኔው 50 ሺህ ብር አሁን ላይ ስንት ይሆን ???


የሕይወቴ_ታሪክ

(ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተ/ማርያም)

አዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ
Via Book for all

Exit mobile version