Site icon ETHIO12.COM

በአማራ ክልል የመንግሥት ተቋማት መደበኛ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተገለጸ

 አሸባሪው ሕወሓት የፈጸመውን ወረራ ተከትሎ የቀረበውን የኅልውና ትግል ጥሪ ለመደገፍ መደበኛ አገልግሎት አቋርጠው የነበሩ የመንግሥት ተቋማት መደበኛ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ከኅልውና ትግሉ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ከተወሰኑ ተቋማት በስተቀር ሁሉም በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት መደበኛ አገልግሎታቸውን አቋርጠው የኅልውና ትግሉን በተለያየ መልኩ ሲደግፉ መቆየታቸውን የቢሮ ኃላፊው ግዛቸው ሙሉነህ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ የኅልውና ዘመቻው መልክ እየያዘ ስለሆነና አብዛኞቹ ቦታዎችም ከወረራ ነጻ ስለወጡ ተቋማት መደበኛ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ነው ያሉት፡፡

ከውስን ቦታዎች ውጭ አብዛኞቹ አካባቢዎች ከአሸባሪው ቡድን ነጻ የወጡ በመሆኑ የክልሉ ምክር ቤት አጠቃላይ ሁኔታዎችን ገምግሞ ውሳኔው እንዲቀየር ማድረጉን ያስታወሱት ኃላፊው ውሳኔው ታሳቢ ያደረገውም ሌሎች ሥራዎች እንዳይጎዱና ኢኮኖሚውም እንዳይቀዛቀዝ በሚል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ሁሉም የመንግሥት ተቋማትና ሠራተኞች ከመደበኛ ተግባራቸው ጎን ለጎን የኅልውና ዘመቻውን መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡

እንደ ኢፕድ ዘዘገባ በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ተይዘው የቆዩ አካባቢዎች ብዙ ነገራቸው የተጎዳ በመሆኑ ሠራተኞች ድሉን የበለጠ ለማጠናከርና ጉዳቱን ሊያካክስ በሚችል ሞራልና ተነሳሽነት ሥራ መጀመራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም በመልካም አስተዳደር፣ በኢኮኖሚው ዘርፍና በማኅበራዊ ዘርፍ ያሉ ሥራዎች ላይ ክልሉን ሊለውጥ በሚችል ደረጃ እንደተቀጣሪ ሳይሆን የባለቤትነት ስሜት ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

የክልሉን ሠላምና ፀጥታ ለመጠበቅና ኅብረተሰቡን በሁሉም መስክ ለመለወጥ በሚሰራው ሥራ ላይ የመንግሥት ሠራተኞች ሚና ትልቅ በመሆኑ ሁላችንም የተጣለብንን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ via – walata


Exit mobile version