ETHIO12.COM

አሸባሪው ሕወሓት ጅምላ ጭፍጨፋ ማካሄዱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አስታወቀ

የሕወሓት ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች ህጻናትንና ሴቶችን ሳይለይ በጅምላ ዘግናኝ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙንና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በተለያዩ አካባቢዎች በንጹኃን ዜጐች ላይ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ዘገባ ይፋ አድርጓል። በሰሜን ወሎና በደቡብ ጎንደር፣ በአፋር ክልል፣ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በአማራ ክልል ኦሮሞ ልዩ ዞን እና በደቡብና በሰሜን ጎንደር ዞኖች ላይ በመዘዋወር የመስክ ምርመራ ስራ በማድረግ በሕወሓት ቡድን የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ ውድመቶችንና ዘረፋዎችን ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ዋና ዳይሬክተር ዳን ይርጋ እንደገለጹት፤ ጉባኤው በአፋርና በአማራ ክልሎች ባደረገው ጥናት የሕወሓት ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች በርካታ ንጹሃን ደፍሯል፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፣ አፈናቅሏል፣ በጅምላ በመግደል፤ በጅምላ ቀብሯል፣ የእምነት ተቋማትን አቃጥሏል፣ዘርፏል፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አሰቃቂ ተግባር መፈጸሙን ምርመራ ባካሄድንባቸው አካባቢዎች ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።

የመስክ ምርመራ ውጤቱ እንደሚያሳው በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተከስተዋል። በዋናነት ንጹሃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ ፈጽሟል። በጅምላ ህጻናትን ፤ አዛውንቶችንና ሴቶችን ያልለየ ዘግናኝ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል። አሸባሪው ቡድን ከባድ መሳሪያዎችን ወደ ንጹሃን መጠለያ ካምቦች ላይ በመተኮስ የንጹሃን ሕይወት እንዲያልፍ አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።

በርካታ የሆኑ ሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር እንደተፈጸመ የምርመራ ውጤታችን አረጋግጧል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ የጤና ተቋማትን፣ ባንኮችንና በርካታ የመሠረተ ልማቶችን አውድመዋል፤ ዘርፈዋል። የዚህ ድርጊት ፈጻሚ የሆነው የሕወሓት ታጣቂ ቡድን ምንም ልዩነት ሳያደርግ በህጻናት፣ በሴቶችና የሕብረተሰብ መገልገያ በሆኑ ተቋማት ላይ ጥቃት ፈጽሟል።

በሕወሓት ቡድን ጥቃት ሳቢያ ከቀያቸውና ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ በርካታ ዜጎች አሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በመጠለያ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በበርካታ አካባቢዎች ላይ ሊበረታታ የሚችል የሰብዓዊ ድጋፍ እየደረሰ ቢሆንም ካለመቀናጀትና ካለመናበብ የተነሳ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በተደጋጋሚ እርዳታ ሲደርስ በተቀሩት ላይ ደግሞ እርዳታ ያለመድረስ ሁኔታ ይስተዋላሉ ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በሕወሓት ቡድን የወደሙ ተቋማትን በፍጥነት መልሶ መገንባት ያስፈልጋል። በተለይ የትምህርት ተቋማት፣ የጤና ተቋማትና በርካታ የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ሁሉም ባለድርሻ አካል ተረባርቦ መስራት አለበት ብለዋል።

 በቀጣይ በሚደረጉ የምርመራ ዘገባዎች ላይ ሰፊ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የንብረት ውድመቶች እንዳሉ መረጃ ያመላክታሉ ያሉት አቶ ዳን፤ ኢሰመጎ ምርመራውን ይቀጥላል፤ መረጃዎችንም እያሰባሰበ የመጨረሻ የምርመራ ውጤት ይፋ ያደርጋል ሲል አዲስ ዘመን ኮሚሽኑን ጠቅሶ አመልክቷል።


Exit mobile version