Site icon ETHIO12.COM

መስቀል አደባባይን መጠቀምን ተከትሎ “በመሪዎች ላይ የሚደረገው ዛቻ ይቁም‼️” የሚል የህግ ጥያቄ ተነሳ

የመስቀል አደባባይን መጠቀምን ተከትሎ እየተሰነዘረ ላለው ዛቻ የኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሰራ አመራር በማህበራዊ ገጹ ” መሪዎቻችን ላይ የሚደረገው ዛቻ ይቁም” በሚል ዕርእስ ባሰራጨው መግለጫ መስቀል አደባባይ በርካታ ዓይነት ዝግጅቶች የሚደረጉበት ቦታ መሆኑን አስታውሶ፣ ይህን አደባባይ ማንም ዜጋ በነጻነት አቅዶና ህግ አክብሮ ሊጠቀምበት እንደሚገባ አሳስቧል።

ይሁን እንጂ “የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች የሆንን ከታሪካዊቷ የኦርቶዶክስ እምነት እና ተከታዮች ጋር አብሮ ከመስራትና በጋራ በአገራዊ ጉዳይ ላይ ከመሳተፍ ባለፈ ግጭትም ይሁን ሌላ የተለየ ፍላጎት እንደሌላት ግልጽ ነው” ሲል መግለጫው አመልክቶ የስብሰባውን ዓላማ በመቀየር የተለየ ቅስቀሳ በመጀመር ደም ለማፋሰስ እየሰሩ ያሉትን ክፍሎች በህግ እንደሚጠይቅ አመልክቷል።

“በማህበራዊ ድህረ ገጽ የአደባባይ ፕሮግራሙን ወደ ሌላ አጀንዳ ሊቀይሩ የሚፈልጉ ጥቂት ግለሰቦች ግን ፕሮግራሙን ከታሠበበት መንፈስ ውጪ የቦታ ጥያቄ አድርጎ በመጠምዘዝ ደም መፋሰስ እንዲፈጠርና በኅብረታችንም አመራሮች ላይ ዛቻ እያደረጉ መሆኑ ስለተደረሰበት ኅብረቱ እነኚህን ጉዳዮች ተመልክቶ በሕግ እንደሚጠይቅ ማሳወቅ ይወዳል”ሲል መግለጫው አመልክቷል።

በመግለጫው በዝርዝር ባይቀርብም ቄስ ምህረተአብ የሚባሉ ከተወሰኑ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ቦታው የኦርቶዶክስ ነው፣ የታጠነ ቅዱስ ቦታ ነው። ኦርቶዶክሳዊያን ውጡ፣ ሞትን አንፈራም፣ ነገ ወደ ስፍራው አቅና። እስር አንፈራም። ወዘተ በሚል ሲቀሰቅሱ የሚያሳይ ፎቶ አሰራጭተዋል። ቪዲዮውን አንድ ሰው ቢያንስ ለ1000 እንዲያሰራጭ ሲያዙ ተሰምተዋል። ይህን የማያደርጉትን የአባቶቻቸው አጥንት ሾህ ሆኖ እንደሚወጋቸው አስታውቀዋል።

“ጴንጤ መስቀል አደባባይን እወስዳለሁ” የሚል መሪ መፈክር ያለበት ቅስቀሳ ይህን ይመስላል።

ቅዳሜ፣ ታሕሳስ 30 ቀን 2014 ዓ.ም

“በመሪዎች ላይ የሚደረገው ዛቻ ይቁም‼️”

እንደሚታወቀው የመስቀል አደባባይ በታሪኩ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኃይማኖታዊ እና የተለያዩ በዓላት የሚደረጉበት አደባባይ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ ለዚህም ማሳያ እስከዛሬ በአደባባዩ የተደረጉ የመስቀል በዓል፣ ህዝባዊ ሠልፎች፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ የመዝናኛ ዝግጅቶች፣ መንግስታዊ ፕሮግራሞች፣ የኢሬቻ በዓል፣ የኢድ አል-ፈጥር በዓል እንዲሁም ሰሞኑን እያየን እንዳለነው ባዛር ከብዙዎቹ በጥቂቱ ናቸው፡፡

የወንጌል አማኙም ማሕበረሰብ ይህ ከበዓላት አልፎ ተርፎ እንደ ፓርክ እየተጎበኘ እና ሕብረተሰቡ እየተዝናናበት የሚገኘውን አደባባይ መጠቀም የዜግነት መብቱ መሆኑ መታመንም መከበርም እንደሚኖርበት የኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በጽኑ ያምናል፡፡

በመሆኑም ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም የሚደረገው ፕሮግራም በተፈጥሮም ይሁን በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ የሚሰበሰብበት ብሎም ለአገራችን የምልጃ ፀሎትን የምናደርግበትና አምላካችንን የምናመልክበት ቀን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች የሆንን ከታሪካዊቷ የኦርቶዶክስ እምነት እና ተከታዮች ጋር አብሮ ከመስራትና በጋራ በአገራዊ ጉዳይ ላይ ከመሳተፍ ባለፈ ግጭትም ይሁን ሌላ የተለየ ፍላጎት እንደሌላት ግልጽ ሆኖ ሳለ፥ በማህበራዊ ድህረ ገጽ የአደባባይ ፕሮግራሙን ወደ ሌላ አጀንዳ ሊቀይሩ የሚፈልጉ ጥቂት ግለሰቦች ግን ፕሮግራሙን ከታሠበበት መንፈስ ውጪ የቦታ ጥያቄ አድርጎ በመጠምዘዝ ደም መፋሰስ እንዲፈጠርና በኅብረታችንም አመራሮች ላይ ዛቻ እያደረጉ መሆኑ ስለተደረሰበት ኅብረቱ እነኚህን ጉዳዮች ተመልክቶ በሕግ እንደሚጠይቅ ማሳወቅ ይወዳል፡፡

የኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሰራ አመራር
ቅዳሜ፣ ታሕሳስ 30 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ።


Exit mobile version