Site icon ETHIO12.COM

በገቢ ማሰባሰቡ ከአርባ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይጠበቃል

በነገው እለት በሸራተን አዲስ በሚጀመረው የእራት ግብዣና የገቢ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ከአርባ ሚሊዮን ዶላር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስታወቀ።

የድርጅቱ ፕሬዚዳንትና የቲያትር ጥባባት ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ጋሻው ሽባባው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት ከኢትዮ ቴሌኮም፤ ዩኒቲ ፎር ኢትዮጵያና ሌሎች ጋር በትብብር በነገው እለት በሸራተን አዲስ ይጀመራል። 

መርሃ ግብሩ ተከታታይነት የሚኖረው ሲሆን ከአርባ ሚሊዮን ብር በላይ ይገኝበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። በመርሃ ግብሩ በተከታታይነት ከሚከናወኑት ሁነቶች መካከልም የትኬት ሽያጭ፤ ከባንኮች ጋር በተደረገ ስምምነት የቀጥታ የገንዘብ ድጋፍና ቴሌቶን መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በፕሮግራሙ የሚሰበሰበው ገቢ በጦርነቱ ለተጎዱት በአፋርና አማራ ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች ለቁሳቁስና የምግብ ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም በጦርነቱ የወደሙ ሃያ የጤና ተቋማትና ሃያ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የታቀደ መሆኑንም ተናግረዋል። 

በመርሃ ግብሩ ላይ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ባለሀብቶች እንዲሁም የኪነጥበብ ባለሙያዎች የሚገኙ ሲሆን፤ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴና ሌሎችም መርሃ ግብሩ ላይ በዙም ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ 

አዲስ ዘመን ጥር 8 ቀን 2013 ዓ.ም

Exit mobile version