Site icon ETHIO12.COM

ኮሜርሻል ኖሚኒስ የኤፈርት ንብረቶችን የማስተዳደሩን ስራ ተረከበ  

የኤፈርት የንግድ ኩባንያዎችን ኮሜርሻል ኖሚኒስ እንዲያስተዳደራቸው መደረጉና ውሳኔውም አቃቤ ህግ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት መፈጸሙ ተሰምቷል። ኮሜርሻል ኖሚኒስ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የበላይነት የሚመራ ሃብት የቋም መሆኑ ይታወቃል።

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር የንግድ ኢምፓየር የሆነውና አቶ ስብሃት ነጋ ከአፍሪካ አንደኛ እንደሆነ የመሰከሩለት ኤፈርት፣ በባለቤቱ አማካይነት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ወረራና ጦርነት መክፈቱን ተከትሎ አቃቤ ህግ ሰላሳ ስምንት በሚሆኑት የኤፈርት እህት ኩባንያዎች የባንክ ሂሳብ እንዲታገድ አስወስኖ ነበር። ኩባንያዎቹ ከህወሓት ጋር ያላቸውን የወንጀል ግንኙነት ላይ ምርመራ እስኪጠናቀቅና ይፋ እስኪሆን ነበር እግዱ የተወሰነው።

በመሃል አገር በመሰረተው የንግድ ኢምፓየር አማካይነት ጦርነቱን እንደሚደጉም መረጃ እንዳለው መንግስት ጠቅሶ አካውናታቸውን እንዲታገድ የተደረጉትን የኤፈርት ድርጅቶች፣ መንግስት በሰየማቸው ስባት አባላት ያሉት ቦርድ እየተዳደረ ቆይቷል። ዋዜማ “ሰማሁ” ሲል ምንጮቹን ሳይገልጽ እንዳለው ከሆነ ሰባቱ መንግስት የሰየማቸው የቦርድ አባላት በፈቃዳቸው ለቀዋል። ይሁን እንጂ የመልቀቃቸው ጭብጥ ምክንያት በዜናው አልሰፈረም። የቦርድ አባላቸው መልቀቃቸው በተገለጸበት የዋዜማ “የሚስጢር ዜና” የተጠቆመው ኮሜርሻል ኖሚኒስ የተሰኘው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስር የሚተዳደረው ተቋም ኤፈርትን እንዲያስተዳድር መደረጉ ነው።

“የቦርዱ አባላት ከሐላፊነታቸው ለመነሳት መልቀቂያ ያስገቡበትን ምክንያት ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም” ሲል ዋዜማ ጽፏል። አስከትሎም “…የፍትህ ሚኒስቴር የኤፈርት ድርጅቶች ጉዳይ ከዳር እስኪደርስ የሚያስተዳድራቸው አካል እንዲሾም ለፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታ መሰረት ኮሜርሻል ኖሚኒስ የማስተዳደሩን ስራ እንዲረከብ ትእዛዝ ተሰጥቷል” ብሏል።

የኤፈርት ኩባንያዎችን ሲመራ የነበረው ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር በጸጋዩ በርሄ እንደነበሩ ይታወሳል። ይህ ዜና እስከታተመ ድረስ አቃቤ ህግም ሆነ አግባብ ያለው ህጋዊ አካል በይፋ የሰጡት መረጃ የለም። የፍትህ ሚኒስቴር ጉዳዩን እንዲያብራራ ሞክረን አልተሳካም። ይሁን እንጂ ሃላፊነቱ ለኮሜርሻል ኖሚኒ የተሰጠው በሚስጢር እንዳልሆነና በገሃድ በግህጋዊ አግባብ እንደሆነ ስማቸው ለጊዜው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የህግ ባለሙያ አመልክተዋል። በቅርቡም ማብራሪያ ይሰጥበታል ብለው እንደሚያምኑ አመልክተዋል።

Exit mobile version