Site icon ETHIO12.COM

የፓን አፍሪካኒዝም ጅማሮ እና የኅብረቱ ግብ

የፓን አፍሪካኒዝም ጅማሮ እና የኅብረቱ ግብ

በቁምነገር አሕመድ

ጥር 23/2014 (ዋልታ) እንደ አውሮፓውያኑ የጊዜ ቀመር በ1812 በምዕራብ ቨርጂኒያ ግዛት ቻርለስ እንደተወለደ ታሪክ የሚያወሳን ማርቲን ሮቢን ሰን ዴላኒ፤ አባቱ በቅኝ አገዛዝ ዘመን ከአፍሪካ አኅጉር በባርነት የተወሰደ ሲሆን፤ የግለሰቡ ልዩ መታወሻው ጥቁር አሜሪካዊያን ወደ አኅጉራቸው አፍሪካ እንዲመለሱ የሚያበረታታ ንቅናቄን ማስጀመሩ ነበር፡፡

በአሜሪካን ወታደራዊ ተቋም ውስጥ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊ ሹም የነበረው ዴላኒ፤ በዘመኑ የነበረው የባርነት ቀንበር እና የጥቁር የበታችነት አሳሳቢ እና ተሰፋ የሚያስቆርጥ ስለመሆኑ ደጋግሞ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲያነሳ ተደምጧል፡፡

የእርሱ አቋም ይህን ያህል ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን ያስቻለው ቤተሰቦቹ ለልጃቸው ከቆዳ ቀለም ማንነታቸው ያለፈ ሐሳብ እና ማንነት እንዲይዝ አድርገው ማሳደጋቸው ነው፡፡ ከ200 ዓመታት በፊት ወደዚህች ምድር የመጣው ማርቲን ዴላኒ የባሪያ ንግድን የሚቃወም፣ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች፣ የህክምና ባለሙያ፣ ወታደር፣ ጋዜጠኛ እና የጥቁር ነፃነት አቀንቃኝ ነበረ፡፡

ማርቲን በበርካታ የጥቁር ነፃነት ንቅናቄዎች ላይ ተሳታፊ ነበር፡፡ በአሜሪካ ውስጥ በየሳምንቱ ይታተም በነበረው ዘ ሚስትሪ ጋዜጣ ላይ ያለ ማቋረጥ ይጽፍ የነበረው ማርቲን ከኒውዮርኩ የጥቁር መብት ተሟጋች ፍሬድሪክ ዳግላስ ጋር ዘ ኖርዝ ስታር በሚል በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈ ስለ ጥቁሮች ነጻነት እና እኩልነት የሚሞግት ጋዜጣ ማሳተም ጀመሩ፡፡

ይህ በትንሹ የተጀመረው ጥረታቸው ቀጥሎ ከ1865 እስከ 1872 የጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊያን የነፃነት ቢሮ Freedmen’s Bureau በመምራት ከ4 ሚሊዮን የሚበልጡ ጥቁር አሜሪካዊያን ከባርነት ነፃ እንዲወጡ አድርጓል፡፡

ልክ እንደ ማርቲን ሁሉ ዛሬ ለበርካታ አፍሪካዊያን ቀና ብሎ መሄድ እና ለጥቁሮች እኩልነት በታገለ የፓን አፍሪካኒዝም ፅንሰ ሐሳብ አራማጅ በመሆን የአሌክሳንደር ኩርሜል ስም ይነሳል፡፡

በ1819 በኒውዮርክ የተወለደው አሌክሳንደር ኩርሜል በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ሲሆን በ1853 ወደ ሊቢያ በመሄድ የሰው ልጅን እኩልነት እና የጥቁሮችን ነፃነት የሰበከ የፓን አፍሪካ ንቅናቄ መስራች እና አራማጅ ነበር፡፡

ለ20 ዓመታት በሊቢያ በቆየበት ወቅት አሌክሳንደር አፍሪካዊያን አንድ ሐሳብን በማንገብ ለነፃነታቸው እንዲቆሙ ሰርቷል፡፡ አፍሪካዊያን ለአፍሪካ የሚል ፅንሰ ሐሳብ በማራመድም እሱን ተክተው ለንቅናቄው ፈርጥ ለሆኑት እነ ማርከስ ጋርቬይ፤ ፓወል ላውረንስ ዱንባል እና ዱ ቦንሲ መንገድ ከፍቷል፡፡

በዚህ መልኩ የተቀጣጠለው የጥቁሮች የነፃነት ማዕበል እየላቀ ሄዶ በ1980 የጥቁሮች ትግል የብሔርተኝነት (ናሽናሊዝምን) አስተሳሰብ እና መርህ ይዞ ንቅናቄውን ዓለም ዐቀፋዊ እንዲሆን ተደረገ፡፡

አዲሱ የብሔርተኝነት አስተሳሰብ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓ ኅብረት እንዲሁም ራሱን ከአውሮፓ ኅብረት ያገለለው የአውሮፓ ፖለቲካል ዶክትሪን እንዲመሰረት ምክንያት ሆኗል፡፡ የኋላ ኋላም በ1920 በዓለም ላይ ሰላምን ለማስፈን እና አገራት የእርስ በእርስ ጦርነትን ለማራቅ በፓሪስ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ መቋቋም ምክንያት ሆኗል፡፡

አፍሪካዊያን ለነፃነታቸው በታገሉባቸው ዓመታት ውስጥ አንድነታቸውን ለማጠናከር ፓን አፍሪካኒዝም የላቀ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ ንቅናቄውን የጀመሩት የመጀመሪያዎቹም ቢሆኑ አፍሪካ አንድ ሆና ማየትን ከመሻት በመነጨው ህልማቸው ውስጥ ከባርነት እና ቀኝ ግዛት ነፃ ከመውጣት ባሻገር ተያይዞ ማደግን እና ከድህነት አዘቅት ውስጥ መውጣትን አስበው ነበር፡፡

ፓን አፍሪካኒዝም አፍሪካዊያን እንዲሁም ከአፍሪካ የተሰደዱ ሁሉ ተመሳሳይ ፍላጎት አላቸውና አንድ ሊሆኑ ይገባል የሚልን ሐሳብ ያራምዳል፡፡

ፓን አፍሪካኒዝም ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን፣ ዩዌሪ ሞሶቬኒ፣ ኩዋሜ ንክሩማህን፣ ሞአመር ጋዳፊን ብሎም ቶማስ ሳንካራን እና ሌሎች ለአፍሪካ አንድነት የቆሙ አፍሪካዊያንን አፍርቷል፡፡

እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር ሐምሌ 9/2002 በደርባን ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ኅብረት ሲመሰረት ይህንን የአንድነት ስሜት አንግቦ ነው፡፡ አፍሪካ ለአፍሪካዊያን ትሆን ዘንድ አፍሪካዊiያን ደግሞ ባላቸው እና በሚኖራቸወ ሁሉ ለአፍሪካ እንዲቆሙ በመጠየቅ የፓን አፍሪክኒዝም ፅንሰ ሐሳብ ዛሬም እንዲዳብር ሆኗል፡፡

በአፍሪካ ኅብረት በርካታ ሐሳቦች ይስተናገዳሉ፡፡ ለአፍሪካ እና አፍሪካዊያን የሚበጁ ቴክኖሎጂ፣ የባሕል እና የሳይንስ የልህቀት ትስስሮች ይመሰረታሉ፡፡

በ2022 ከጦርነት እና ሰላም እጦት ነፃ ለመሆን፣ ከርሃብ እና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ እምርታዊ ለውጥ የምታስመዘግብ፤ በአዲስ አስተሳሰብ አዳዲስ ግቦችን የተለመች አፍሪካን ለመገንባት መሪዎቿ በኅብረቱ መዲና አዲስ አበባ ጉባኤያቸውን ያደርጋሉ፡፡

በዚህ ስብሰባቸው ሥርዓተ ምግብና የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ጉዳይ ለአኅጉሪቱ የሰው ኃይል፣ ማኅበራዊና ምጣኔሃብታዊ ልማቶችን ለማላቅ ሚናው ቁልፍ መሆኑን ለማጠየቅ ‹‹የአፍሪካ አኅጉርን የሥርዓተ ምግብ አቅም መገንባት የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ልማትን ያፋጥናል!›› በሚል መሪ ቃል ይመክራሉ፡፡

አለፍ ሲልም በአጀንዳ 2063 የተያዙ ግቦችን ገቢራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ፍኖተ ካርታዎች ገቢራዊነታቸው እንዴት እየሄደ ነው የሚለው እየተመዘነ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ፡፡

Via WALTA

Exit mobile version