Site icon ETHIO12.COM

ኢሰመኮ ከረዩ የተፈጸመውን ግድያ ህጋዊ ታጣቂዎች እንደፈጸሙት አስታውቀ፤ ሪፖርቱ አስደንጋጭ ሆኗል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ህዳር ወር በመንግስት የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት በግዳጅ ወደ ጫካ ቦታ ተወስደው፤ ጭካኔ በተሞላው ሁኔታ በጥይት ተመተው መገደላቸውን አስታወቀ። የመንግስት የጸጥታ እና የአካባቢ አስተዳደር ሰዎች ባሉበት የተደረገው ነው የተባለው ይህ ግድያ፤ ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ስለመሆኑ አሳማኝ ምክንያቶች እንዳሉም ኢሰመኮ ገልጿል። ቀደም ሲል ግድያው በኦነግ ሸኔ አማካይነት እንደተፈጸመ አድርጎ ክልሉ ለሚዲያዎች መረጃ ምስጠቱ ይታወቃል።

ኢሰመኮ ይህን ያስታወቀው፤ በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ግድያ ላይ ያደረገውን ምርመራ የያዘ ሪፖርት ዛሬ ረቡዕ ጥር 25 ይፋ ካደረገ በኋላ ባወጣው መግለጫ ነው። በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ አርዳ ጅላ በተባለ ቦታ ላይ ህዳር 22፤ 2014 የተፈጸመውን ይህን ጥቃት በተመለከተ ጥቆማ የደረሰው ኢሰመኮ፤ በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ በቦታው ላይ በመገኘት ለአምስት ቀናት ምርመራ ማካሄዱን በመግለጫው አመልክቷል።

ግድያው ወደ ተፈጸመበት ቦታ የተጓዘው የኢሰመኮ የምርመራ ቡድን የአይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችን፣ የሟች ቤተሰቦችን እና የከረዩ ማኅበረሰብ የሀገር ሽማግሌዎችን አነጋግሯል ተብሏል። የምርመራ ቡድኑ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ48 ሰዎች ጋር ቃለ መጠይቅ እና የቡድን ውይይት ማድረጉ በምርመራ ሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።

ኢሰመኮ በሪፖርቱ ማጠቃለያ ባቀረበው ምክረ ሃሳብ በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ላይ ይህን የግድያ ወንጀል የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሰዎችን እንዲሁም በፖሊስ አባላት ላይ የግድያና የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል የፈጸሙትን ሰዎች በሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ተገቢው የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስቧል። ለሟቾች ቤተሰቦች እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ለደረሰባቸው ጉዳት ተገቢ የሆነ ካሳ ሊሰጣቸው እንደሚገባም አስገንዝቧል። ዝርዝር ዘገባውን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፦ https://ethiopiainsider.com/2022/5788/ 

Exit mobile version