Site icon ETHIO12.COM

ዲያስፖራው ባደረጋቸው ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎዎች ከ22 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

ዲያስፖራው አገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ወደ አገር ቤት በመምጣት ባደረጋቸው ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎዎች 22 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን የዲያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ በተለይም የዲያስፖራው ወደ አገር ቤት መምጣት በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ዘርፍ ስኬት የተገኘበት ነበር ብለዋል።

ዲያስፖራው ወደ አገር ቤት መምጣቱ የእርስ በእርስ ትውውቅ እንዲኖረው እና የአገር አምባሳደርነቱ አጠናክሮ እንዲቀጥል ያገዘ መሆኑንም ዶክተር መሀመድ አንስተዋል።

ከገጽታ ግንባታ ባለፈም እስካሁን ከቀጥተኛ ተቋማት በተሰበሰበ መረጃ ብቻ ከአየር ትኬት፣ ከአገልግሎት ዘርፎች እና ከቪዛ አገልግሎት 33 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር መገኘቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ለሰብዓዊ ድጋፍ 239 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በድጋፍ መልክ አበርክተዋል።

ዲያስፖራው በአገሩ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ከዘርፍ ተኮር ማብራሪያ ጋር እንዲያገኝ እንዳስቻለውም ተጠቅሷል።

እስካሁን በተጠናቀረ መረጃ መሰረት 450 የዲያስፖራ አባላት የኢንቨስትመንት ጥያቄ አቅርበው ወደ እንቅስቃሴ ገብተዋል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ የቢሮክራሲ ችግሮችን ለመፍታት ተቋማት የጋራ ጥረት እያደረጉ ነውም ተብሏል።

ዲያስፖራው በማዕከልና በክልሎች በተዘጋጁ 55 ሁነቶች ላይ መሳተፉ የተገለጸ ሲሆን÷ ከ”በቃ” የጎዳና ላይ ሰልፍ ውጪ ሌሎቹ መከናወናቸው ዶክተር መሀመድ ተናግረዋል።

ጥሪው ዓመቱን ሙሉ የሚዘልቅ በመሆኑ ተጨማሪ ስኬቶች እንደሚመዘገቡም ይጠበቃል ነው ያሉት።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version