Site icon ETHIO12.COM

የተመድ ዋና ጸሃፊ ከአፋር ርዕሰ መስተዳድር ጥያቄ ቀረበላቸው፤ ትህነግ በአማራና አፋር 1.7 ቢሊዮን የኤሌክትሪክ ውድመት አድርሷል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ ሰመራ የገቡት የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ መሆኑንን ጠቅሶ ሲያበቃ ከክልሉ ውጪ በማለፍ ዳግም ወረራ እያካሄደ ባለበት ወቅት ነው። በአፋር ከሶስት መቶ ሺህ ሕዝብ በላይ በድጋሚ ተፈናቅሎና በከባድ መሳሪያ እንዲያልቅ እየተደረገ ባለበት ሰዓት አሚና ሰመራ መግባታቸውን ተከትሎ ነው ጥሪው በአካል የደረሳቸው።

“ተመድ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ሄደው ያልተመለሱ መኪኖቹ ምን እየሠሩ እንደሆነና የሚላከው ዕርዳታ ለጦርነት ዓላማ ሳይሆን ለንፁሀን ዜጎች ስለመድረሱ ሊያጣራ ይገባል”

አወል አርባ

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች በየጊዜው ጦርነት እየተከፈተበት ላለው የአፋር ሕዝብ ድጋፍ እንዲደረግ ሲጥየቁ ምሬታቸውንም አሰምተዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ አሸባሪው ህወሓት የክልሉን ድንበር ተሻግሮ በአሁኑ ወቅት በአምስት ወረዳዎች ላይ ጦርነት ከፍቶ ንጽሃንን እየጨረሰ መሆኑንና የዓለምን ዝምታ በገሃድ ተናግረዋል።

በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ የተመራ የልዑካን ቡድን ከርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እንዲሁም ከተለያዩ የጎሳ መሪዎች ጋር ወቅታዊ የክልሉን ሁኔታ በተመለከተ ባካሄዱት ውይይት በአፋር ትህነግ ምን እየሰራ እንደሆነ ዘርዝረዋል።

ጦርነት ከተከፈተባቸው ወረዳዎች መካከል በሦስቱ ምንም ዓይነት ጦር ያልሰፈረባቸው እንደነበሩ፣ ጥቃቱ ሆን ተብሎ በንፁሀን መኖሪያ መንደሮች ላይ የተከፈቱ እንደሆነ ገልጸዋል። ጭፍጨፋው ንፁሀን ዜጎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን አወል አርባና በውይይቱ የተገኙ አዛውንቶች መስክረዋል።

አወል አርባ ተመድን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት አፋር ክልል መጥተው ሰብአዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል ስለሚደርስበት መንገድ ከመነጋገር ባሻገር ወረራ የተፈፀመበትን የአፋር ሕዝብ ስለመርዳት እንዲያስቡም አበክረው ጥይቀዋል።

አፋር ሰብአዊ እርዳታዎች ወደ ትግራይ እንዲሄድ መንገድ ከማመቻቸት ጀምሮ ማከማቻ መጋዘኖች እንዲዘጋጁ በማድርገ ገደብ የሌለው ትብብር ሲያደርግ እንደቆየ ያመልከቱት ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ ለትግራይ ሕዝብም ጭምር ጠላት የሆነው አሸባሪው ህወሓት ይህንን ሁሉ ትብብርና ድጋፍ ወደ ጎን በማለት ጦርነት እንደከፈተ አስረድተዋል። በዚህም ሳቢያ ሆን ብሎ የእርዳታ ማስተጓጎል ተግባር መፈጸሙን አመልክተዋል።

አወል አርባ አያይዘውም ተመድን የሚፈትነውን ጥያቄ አቅረበዋል። “ተመድ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ሄደው ያልተመለሱ መኪኖቹ ምን እየሠሩ እንደሆነና የሚላከው ዕርዳታ ለጦርነት ዓላማ ሳይሆን ለንፁሀን ዜጎች ስለመድረሱ ሊያጣራ ይገባል” ሲሉ ትህነግ እርዳታንና እርዳታ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎችን ምን እያደረጋቸውና ልምን ዓላማ እየተጠቀመባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ጦርነቱ በሚቆምበትና ሰላማዊ ውይይቶች በሚኖሩበት ሁኔታ ላይ ይሠራል፤ሰብአዊ ድጋፎች ጦርነት ባለበት በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ንፁሀን እንዲደርስ እንሠራለን

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአፋር ክልል ለሀገር ትልቅ ዋጋ እየከፈለ ያለ መሆኑን ገልጸው ለዚህም ምስጋና ይገባዋል ሲሉ ማወደሳቸውን ያስታወቀው የኢቢሲ ዘገባ የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ ጦርነቱ በሚቆምበትና ሰላማዊ ውይይቶች በሚኖሩበት ሁኔታ ላይ ይሠራል ሲሉ መናገራቸውን አመልክቷል። ሰብአዊ ድጋፎች ጦርነት ባለበት በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ንፁሀን እንዲደርስ እንሠራለን ማለታቸውንም ገልጿል።

በሌላ ዜና አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች በሚገኙ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ከ 1 ቢሊየን 644 ሚሊየን ብር በላይ ውድመት ማድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን በሰጡት መግለጫ ÷ ቡድኑ በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ በፈጸመው ወረራ በህዝብ ሃብት ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል ብለዋል፡፡

መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመጠገንት በተደረገው ጥረትም አብዛኞቹ የአማራ እና የአፋር ክልሎች የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘታቸውን ነው የገለጹት።

የወደሙ እና ዝርፊያ የተፈጸመባቸውን መልሶ በመጠገን የኅብተረሰቡን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ተደርጓል ያሉት ዳይሬክተሩ÷ የወደመውን መሠረተ ልማት አሟልቶ ወደ ቀደመ አቅሙ ለመመለስ 23 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በተጠቀሱት አካባቢዎች 53 ነጥብ 3 በመቶ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ውድመት ማድረሱም ፋና ተቋሙን ጠቅሶ አመልክቷል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

Exit mobile version