ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ በዶላር ሳይሆን በብር የኪራይ ውል የምትጠቀምበት ስምምነት ጫፍ እየደረሰ ነው

ኢትዮጵያና ኤርትራ በመካከላቸው የነበራቸውን “የጸብ ግድግዳ” ካፈረሱ በሁዋላ በርካታ የንግድና የጋራ ልማት ስምምነቶችን ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮቹ በሁለቱም ወገን ሲጠቅሱ ማቆየታቸው ይታወሳል። የዛጎል ታማኝ የመረጃ ሰው እንደገለጹት በሚስጢር ሲደረጉ ከነበሩት ስምምነቶች ውስጥ አንዱ አሰብን በዶላር ሳይሆን በብር የመጠቀሙ ጉዳይ ነው።መነሻ ምክንያቶቹ ሁለት እንደሆኑ ያስረዱት የመረጃው ሰው፣ አንደኛ ኤርትራ ከኢትዮጵያ በርካታ ግብአቶች ትፈልጋለች። በነጻ የንግድ ስምምነት በብር ትገዛለች።

ሁለተኛው ምክንያት ኤርትራ በብር በርካታ ገብአቶችን የምትገዛ ከሆነ የኢትዮጵያ ብር ያስፈልጋታል። ስለዚህ ከወደብ ኪራይ ብር ከኢትዮጵያ ታገኛለች።ጥቅሙ በቀናነት ከታየ ለሁለቱም አገር ሕዝብ ጠቃሚ ስለሆነ ብዙም ክርከር አያልነበረው የስምምነት አካል ቢሆንም በህወሃት በኩል በነበረው ሴራ አማካይነት ወደ ተግባር መግባት እንዳልተቻለ ነግረውናል። በምርጫ ዋዜማ በርካታ ጉዳይ ማንሳቱ አግባብ ስለልሆነ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ያለገቡት መረጃ አቀባያችን ” ዛሬ ይፋ የሆነው ዜና የዚሁ አካል ነው” ሲሉ አስታወቀዋል።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ቡና ሸጣ የምታገኘውን ምንዛሬ ለጅቡቲ ስታስረክብ መኖር ከጀመረች ሃያ ዓመታት አልፈዋል። ዜናው ከታች ያለው ነው።ኢትዮጵያን ከኤርትራ የአሰብ ወደብ ጋር የሚያስተሳስረው የሜሎዶኒ መገንጠያ – ማንዳ – ቡሬ የመንግድ ግንባታ ፕሮጀክት በመንግሥት በተመደበ 2 ነጥብ 08 ቢሊዮን ብር በአስፋልትና በሲሚንቶ ኮንክሪት ደረጃ ግንባታው ተጀመረ፡፡

የትራንስፖርት ሚንስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሀጂ አወል አርባ፣ የትራንስፖርት ሚንስቴር ድኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ሀብታሙ ተገኘ እንዲሁም ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ የፕሮጀክቱ መገንባት የአሰብ ወደብ መዳረሻ የሆነው የሜሎዶኒ መገንጠያ – ማንዳ – ቡሬ መንገድ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለሚኖረው የንግድ ትስስር መጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽን የሚያበረክት መንገድ ከመሆኑም በላይ ማህበራዊ መስተጋብሩን የሚያዋህድ ነውም ብለዋል ።የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው መንግስት በክልሉ ብሎም በሀገራችን ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ በተሻለ ጥራትና ብቃት እያካሄደ ይገኛል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ከተቀረው አለም ጋር ለሚኖራት የወጩ ገቢ ንግድ ተጨማሪ የአሰብን እና የታጁራ ወደብን ለመጠቀም የሚያስችላትን እድል መፍጠር የተቻለበት ታሪካዊ እለት ነው ሲሉም ገልጸዋል።አቶ አወል የመንገድ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ችግር እንዳያጋጥም ጥብቅ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል።የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ሀብታሙ ተገኘ በበኩላቸው የሜሎዶኒ መገንጠያ – ማንዳ – ቡሬ ፕሮጀክት 71 ነጥብ 65 ኪ.ሜትር እርዝመት ያለውና በመንግሥት በተመደበ 2 ነጥብ 08 ቢሊዮን ብር በአስፋልት እና በሲሚንቶ ኮንክሪት ደረጃ የሚገነባ ነው ብለዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ በውሉ መሰረት በ3 ዓመት ከ6 ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ የባለስልጣኑ መ/ቤት አስፈላጊውን ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል ።የሜሎዶኒ መገንጠያ – ማንዳ – ቡሬ ዲዛይና ግንባታ ፕሮጀክት የሚገነባው ሻንዶንግ ሊኪኖ ግሩፕ በተሰኘ የቻይና አለማቀፍ ድርጅት ነው። የመንገዱን ጥራት በመቆጣጠር ረገድ ስሜክ ኢንተርናሽናል እንዲሁም ቫሊዩ ኢንጅነሪንግ በንዑስ ተቋራጭነት እንደሚሳተፉ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

    Leave a Reply