“ዳጉ” ስውሩ ጦር – የፕሮፓጋንዳ ምች

“ዳጉ” የሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይልን የሐሰት ፕሮፓጋንዳን ከመመከት አልፎ እንቅስቃሴውን በማክሸፍ የጎላ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው የአፋር ባህላዊ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት “ዳጉ” የሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይልን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ከመመከት አልፎ እንቅስቃሴውን በማክሸፍ የጎላ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አወል አርባ ገለጹ።

የሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ፍላጎቱን ለማሳካት በሀገር ላይ እየፈጸመ ለሚገኘው ክህደት የትግራይ ሕዝብ መጠቀሚያ መሆን አይገባውም ብለዋል።
የማዕድን ሚኒስቴር በጦርነቱ ለተጎዱ ተቋሞች መልሶ ግንባታ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ዛሬ አበርክቷል።

የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አቶ አወል አርባ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ‘ታላቋን ትግራይ ለመመስረት ኢትዮጵያን ማፍረስ አለብኝ’ ብሎ ያለ የለሌ ኃይሉን አሟጦ የግፍ ጦርነት አውጇል።

በአፋር ግንባር ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል በዋናነት የሀገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ መስመርን በመቆጣጠር እንደመደራደሪያ ለመጠቀም አልሞ ያለውን አቅም ሁሉ አሟጦ እየሞከረ መሆኑንም ርእሰ መሥተዳድሩ ጠቅሰዋል።

የአፋር ሕዝብ ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን በቅንጅት የሽብር ቡድኑን የጥፋት ህልም ቅዠት ሆኖ እንዲቀር እያደረጉት ይገኛሉ ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ እንዳሉት በተለይም የጥፋት ቡድኑ ሚሌን ለመቆጣጠር አልሞ በከፈተው ጦርነት በመከላከያ ሠራዊታችን እየደረሰበት ባለው ጠንካራ ምት ተሽመድምዶ እየተፍረከረከ ይገኛል።
በዚህ ግንባር ሕዝቡና ሠራዊቱ የፈጠሩት ጠንካራ ቅንጅትና መናበብ ጠላት መከላከያ ሠራዊቱን ፊት ለፊት ከመጋፈጥ ይልቅ በየጢሻው ተሽሎክሉኮ ለማምለጥ ቢሞክርም አርብቶ አደሩ ሕዝብ እያሳደደ መግቢያ መውጫ እያሳጣው ነው ብለዋል።

አቶ አወል ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል በጦር ግንባር የደረሰበትን ኪሳራ በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ለማደናገር የተለያዩ የውዥንብር መረጃዎችን ለመልቀቅ ቢሞክርም ዳጉን የመሠለ የጠራ አስተማማኝ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ባለቤት የሆነው የአፋር ሕዝብ ለዚህ ቦታ እንደለሌው በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
የዳጉ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት ባለቤት የሆነው የአፋር አርብቶ አደር በጦርነቱ ተደናግጦ ከቤቱ ከመሸሽ ይልቅ በአካባቢው ተረጋግቶ ራሱን እየተከላከለ የጠላትን እንቅስቃሴና ተያያዥ መረጃዎችን ለወገን ጦር ፈጥኖ በማድረስ ጠንካራ ሕዝባዊ ደጀንነቱን አስመስክሯል ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንደዚህ ዓይነት የሕዝብ ድጋፍ ካለው ለሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ብቻ ሳይሆን ለውጭ ወራሪዎችም የማይመለስ፣ የማይገፋ ተራራ መሆኑን በአፋር ግንባር ተጋድሎ የሠራዊቱን አኩሪ ገድል በተግባር ዐይተናል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አወል አርባ።
ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈጸመው ጥቃት መጥፎ የማይሽር ጠባሳ እንደተወም ገልጸዋል።

አቶ አወል “የሽብር ቡድኑ የጥፋት ዓላማውን ለማሳካት አቅመደካሞችን እና ሕጻናትን ጨምሮ የትግራይ ሕዝብን በገፍ እንደቅጠል እያረገፈ ይገኛል” ብለዋል።
በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲገለል በማድረግ የጥፋት ቡድኑ ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሳሪያ እያደረገው በመሆኑ ከማንም በላይ ቆም ብሎ ቡድኑን በቃህ ሊለው ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

Leave a Reply