Site icon ETHIO12.COM

ኢኮኖሚው በፈተናዎች ውስጥ እድገት ማሳየቱ


የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፈተናዎች ውስጥ አበረታች እድገት ማሳየቱ መጪው ጊዜ ብሩህ መሆኑን ያመላክታል ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ አስታወቁ።

አቶ ዘመዴነህ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮሮና ምክንያት የዓለም ኢኮኖሚ እድገት ከደረጃ በታች ወረዶ የቁልቁለት ጉዞ ላይ ነው።በዚህ ፈተና ወቅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአራት እስከ አምስት በመቶ ማደጉን የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ። ምንም እንኳ ኮሮና፣የውጭ ጫናና ጦርነት አገራችን ኢኮኖሚ ቢጎዳም በተወሰደው የኢኮኖሚ የማሻሻያዎች ጫናዎቹን ተቋቁሞ እድገት ማስመዝገቡ መጪው ጊዜ ብሩህ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

በኑሮ ውድነት ምክንያት ለአንዳንዶቹ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ኢኮኖሚ እድገቱ ትርጉም አልባ መሆኑ አያጠራጥርም ያሉት አቶ ዘመዴነህ፤ ኑሮ ውድነቱን ለማርገብም አኳያ መንግሥት መሠረታዊ ሸቀጦችን በድጎማ ማቅረቡና ለመስኖ ስራዎች የሰጠው ትኩረት እንደ ቀላል የሚታይ እንዳልሆነ ለተመዘገበው እድገትም መሰረት መጣሉን …ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ከመቻል አልፋ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን የጠቆሙት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ወደ ምርት የገቡት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በግብርና ምርት ላይ እሴት በመጨርመር በዓለም ገበያ ተፈላጊ ምርቶችን በማቅረብ ያስገኙት ገቢ አበረታችና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ አቶ ዘመዴነህ ገለጻ፣የኮሮና ወረርሽኝና ጦርነቱ ባይከሰቱ ኖሮ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት አሁን ከተመዘገበው እጥፍ በላይ ሊሆን ይችላል። በኢኮኖሚው ላይ የኮሮና አሉታዊ ተጽእኖ ከዚህ በፊት እንደነበረው ስለማይቀጥልና ያጋጠመን ጦርነትም እየተገባደደ በመሆኑ ኢኮኖሚው አሁን ከተመዘገባው ዕድገት በላይ በመጪዎቹ ዓመታት የሚያድግበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል።

ለግብርና ሴክተሩ ብቻ ተገቢ ትኩረት ከተሰጠ ከአምስት በመቶ በላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ይቻላል ያሉት አቶ ዘመዴነህ፤ከማዕድናት በተለይ ከወርቅ እየተገኘ ያለው የዉጭ ምንዛሪ አበረታች በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበትም አመልክተዋል። 

የታለመውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ዳር ከማድረስ ጎን ለጎን ህብረተሰቡ በኑሮ ውድነቱ እንዳይጎዳ ድጎማውን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ አመልክተው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለዋጋ ግሽበቱና ለኑሮ ውድነቱ መንስኤ የሆነውን ገበያ ስርዓቱን ማዘመን ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል። 

ከውጭ የሚገቡ የቅንጦት እቃዎችን በማስቀረት የአገር ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ የመላክ ጅማሮ ማጎልበት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዋቅሹም ፍቃዱ አዲስ ዘመን የካቲት 2/2014

Exit mobile version