Site icon ETHIO12.COM

የንግድ ተላላኪዎች እና እንደራሴዎች በንግድ ስራ ያላቸው ሚና

አንድ ነጋዴ የተሰማራበትን የንግድ ስራ በውጤታማነት፣ በቅልጥፍናና በጥራት ለመስራት እንዲሁም የሚያመርተውን ምርት ወይም የሚሰጠዉን አገልግሎት ለሸማች/ለተጠቃሚዉ በአግባቡ ለማደረስ እንዲያስችለዉ የተለያየ ዘዴዎችን ይጠቀማል፡፡ በዚህ መሰረት የንግድ ሰራተኞችን በስራ ውል ቀጥሮ ማሰራት፣ የንግድ ወኪሎችን በየቦታዉ ማስቀመጥ እንዲሁም ከንግድ ተላላኪዎችና እንድራሴዎች ጋር የሚሰራ ሲሆን በዚህ ጽሑፍ በአዲሱ ንግድ ህጋችን እዉቅና ስላላቸዉ የንግድ ተላላኪዎችና እንድራሴዎች ምንነትና ስራዎቻቸው ተዳሰዋል፡፡

  1. የንግድ ተላላኪዎች፣ የንግድ እንደራሴዎች እና ያላቸው ሚና

1.1. የንግድ ተላላኪዎች
ከላይ እንደተጠቀሰው ነገዴዎች የተለያዩ ሰዎችን በመጠቀም ከሸማቹ ወይም ከአገልግሎት ፈላጊዉ ጋር ከሚገናኙባቸዉ መንገዶች ዉስጥ አንዱ የንግድ ተላላኪዎችን በመጠቀም ነዉ፡፡ በንግድ ህጉ አንቀጽ 36(1) መሰረት የንግድ ተላላኪ ማለት መኖሪያው የንግድ መደብር ዋና መሥሪያ ቤት ባለበት የሆነና ከነጋዴዉ ጋር በተዋዋሉት የሥራ ውል መሠረት ከነጋዴዉ ጋር የሚሠራ፤ ነጋዴዉ እያዘዘው የነጋዴዉ ደንበኞች በሚገኙበት ቦታ እየተዘዋወረ በነጋዴዉ ስምና ምትክ ሆኖ ዕቃ የሚያቀርብ ወይም አገልግሎት የሚሰጥ ሰው ነው፡፡ በህጉ አንቀጽ 36(2) መሰረት የንግድ ተላላኪዎች በነጋዴዉ ስምና ምትክ ሆነው ዕቃ ሲያቀርቡ ወይም አገልግሎት ሲሰጡ በመካከላቸዉ ሌላ የዉል ቃል ከሌለ በስተቀር የንግድ ተላላኪዎች የተዋዋሏቸዉ ውሎች ለነጋዴዉ ቀርበው መጽደቅ ይኖርባቸዋል፡፡

1.2. የንግድ እንድራሴዎች
በንግድ ህጉ አንቀጽ 37 ስር የንግድ እንድራሴዎች መኖሪያቸው የወካዩ ነጋዴ የንግድ ማህበር ዋና መሥሪያ ቤት ባለበት ሥፍራ ያልሆነና ከነጋዴዉ ጋራ በተዋዋሉት የሥራ ውል መሠረት ነጋዴዉ እንዲሠሩ እያዘዛቸው በተወሰኑ ቦታዎች የነጋዴውን ምርቶች እና አገልግሎቶች የሚያስተዋውቁ፣ የገበያ ጥናትና ለነጋዴዉ ሥራ መስፋፋት የሚረዱ ተመሳሳይ ሥራዎች የሚሰሩ ሰዎች እንደሆኑ ትርጉም ተሰጥቷቸዋል፡፡

የንግድ እንድራሴዎች ከንግድ ተላላኪዎች የሚለዩት የንግድ ተላላኪዎች መኖሪያቸው የንግድ መደብር ዋና መሥሪያ ቤት ባለበት በማድረግ በተዋዋሉት የሥራ ዉል መሠረት ከነጋዴዉ ጋር የሚሠሩ፤ ነጋዴዉ እያዘዛቸው የነጋዴዉ ደንበኞች በሚገኙበት ቦታ እየተዘዋወሩ በነጋዴዉ ስምና ምትክ ሆነው ዕቃ የሚያቀርቡ ወይም አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች ሲሆኑ የንግድ እንድራሴዎች ደግሞ የወካዩ ነጋዴ የንግድ ማህበር ዋና መሥሪያ ቤት በሌለበት ቦታ ነጋዴዉ በሚያዛቸዉ መሰረት በተወሰኑ ቦታዎች ላይ የነጋዴዉን ምርቶች እና አገልግሎቶች የሚያስተዋውቁ፣ የገበያ ጥናትና ለነጋዴዉ ሥራ መስፋፋት የሚረዱ ተመሳሳይ ሥራዎች የሚሰሩ ሰዎች ናቸዉ፡፡

1.3. የንግድ ተላላኪዎችና እንድራሴዎች ነጋዴ ስላለመሆናቸው
በአዲሱ የንግድ ህግ አንቀጽ 5 ሥር የተዘረዘሩትንና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎች በቋሚነት ለትርፍ የሚሠሩ ሰዎች እንደ ነጋዴ እንደሚቆጠሩ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ የንግድ ተላላኪዎችና እንድራሴዎችን በሚመለከት ህጉ በግልጽ በአንቀጽ 36(3) እና 37(2) ላይ ነጋዴዎች እንዳልሆኑ አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም የንግድ ተላላኪዎችና እንድራሴዎች ነጋዴ ሳይሆኑ በስራ ዉል ስምምነት በደመወዝ ወይም በኮሚሽን ወይም ሁለቱንም በማጣመር በሚደረግ ክፍያ በነጋዴዉ በሚታዘዙት መሰረት የሚሰሩ ሰዎች ናቸዉ፡፡

  1. በንግድ ተላላኪዎችና እንድራሴዎች ላይ የተጣሉ ክልከላዎች

2.1. የንግድ ተላላኪዎችና እንድራሴዎች የግል ንግድ እንዳይፈጽሙ ስለመከልከላቸዉ
የጥቅም ግጭት እንዳይፈጠር ለመከላከል በማሰብ ህጉ በአንቀጽ 38 ላይ ነጋዴዉና የንግድ ተላላኪዎች ወይም እንድራሴዎች በስራ ውላቸዉ ዉስጥ በግልጽ ካልተስማሙ በስተቀር የንግድ ተላላኪዎችና የንግድ እንድራሴዎች ስለ ራሳቸውም ሆነ ስለ ሌላ ሦስተኛ ወገን ሆነው እነሱን የቀጠራቸው ነጋዴ ከሚሠራው የንግድ ሥራ ጋራ ተመሳሳይ የሆነ የግል ንግድ እንዳይነግዱ ከልክሏል፡፡ ይህንን ክልከላ በመተላለፍ የግል ንግድ ሲነግዱ በተገኙ ጊዜ የሚከተሉት እርምጃዎች እንደሚወሰዱ በአንቀጽ 38(1) እና (2) ተቀምጧል፡፡
• የሚከፈላቸዉን ደመወዝ ወይም ኮሚሽን ወይም ሁለቱንም የመከፈል መብታቸዉን ያጣሉ፡፡
• ዉል እንዳይቀጥል በተሰረዘ ጊዜ ሊያገኙ የሚችሉ ካሳ የመከፈል መብታቸዉን ያጣሉ፡፡
• ቀጣሪዉ አካል/ነጋዴዉ ኪሳራ መጠየቅ ይችላል፣ የስራዉንም ዉል ለመሰረዝ ወይም ዉሉን አላድስም ለማለትም በቂ ምክንያት ይሆናል፡፡

2.2. ለሌሌች ነጋዴዎች ተተክቶ አለመስራት
ተቃራኒ የዉል ስምምነት ከሌለ በስተቀር የንግድ ተላላኪዎችና እንድራሴዎች በውል ግዴታ ለገቡለት ነጋዴ ብቻ እንጂ ስለሌሎች ነጋዴዎች ተተክተው መሥራት የማይችሉ ሲሆን ለሌሎች ነጋዴዎች ተተክተው ሲሠሩ በተገኙ ጊዜ የሚከፈላቸዉን ደመወዝ ወይም ኮሚሽን ወይም ሁለቱንም እንዲሁም ካሳ የመከፈል መብታቸዉን እንደሚያጡ የህጉ አንቀጽ 39 ይደነግጋል፡፡

በውላቸዉ ላይ ለሌሎች ነጋዴዎች ተተክቶ መሥራት እንደሚቻል ከተስማሙ ስለሌሎች ነጋዴዎች ተተክተው መሥራት የሚችሉ መሆኑን ህጉ የፈቀደ ቢሆንም ነገር ግን በምንም አኳኋን ቢሆን ግዴታ የገቡለት ነጋዴ ከሚሸጠው ዕቃ ወይም ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ዕቃ ለመሸጥ ወይም አገልግሎት ለመስጠት ለሌላ ነጋዴ ተተክቶ ለመሥራት እንደማይፈቀድ በአንቀጽ 39(2) ስር በግልጽ ተደንግጓል፡፡

  1. የንግድ ተላላኪዎችና እንድራሴዎች ስላለባቸዉ ሃላፊነትና ተጠያቂነት
    በኢትዮጵያ የፍትሃብሄር ሕግ አንቀጽ 2179 ውክልና ወይም እንደራሴነት አንድም ከሕግ በሌላ መልኩ ደግሞ ከውል ሊመነጭ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ የንግድ ተላላኪዎችና እንድራሴዎች ከነጋዴዉ ጋር በሚገቡት የስራ ዉል መሰረት በነጋዴዉ የሚታዘዙትን ስራዎች ለመስራት የሚስማሙ በመሆኑ ከውል የሚመነጭ የውክልና ወይም የእንደራሴነት ባህሪያት ይኖራቸዋል፡፡ በመሆኑም ከነጋዴዉ ጋርና ከሶስተኛ ወገኖች ጋር ያላቸዉን ግኙነት በተመለከተ ስለ ውክልና/እንድራሴነት የተመለከቱት የፍትሃብሄር ሕግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት እንዳላቸዉ መረዳት ይቻላል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ለአብነት የፍትሐብሔር ህጉ በአንቀጽ 2189(1) ስር እንደራሴዉ ከወኪልነቱ ስልጣን ሳያልፍ በሌላ ሰዉ ስም የመዋዋል ተግባሮችን የፈጸመ እንደሆነ በእርሱ የተፈጸሙት ተግባሮች በቀጥታ በሾመዉ ሰዉ እንደተፈጸመ ይቆጠራል የሚል በመሆኑ አሁን በያዝነዉ ጉዳይ ላይ የንግድ ተላላኪዉ ወይም እንድራሴዉ በነጋዴዉ ስም የሚሰሩ እንደመሆናቸዉ በተሰጣቸዉ ስልጣን መሰረት ወይም በታዘዙት መሰረት የሚፈጽሙት ዉል በነጋዴዉ እንደተፈጸመ የሚቆጠር ይሆናሉ፡፡ ሆኖም ግን ከተሰጣቸዉ ስልጣን ወሰን ዉጪ በማለፍ የሰሩት ስራ ካለ ነጋዴዉ የተፈጸመዉን ተግባር ለማጽደቅ ወይም ለማፍረስ እንደሚችል የፍትሐብሔር ህጉ አንቀጽ 2190(1) ይደንጋገል፡፡

የፍትሐብሔር ህጉ አንቀጽ 2208(1) እንዳስቀመጠው ተወካዩ ከወካዩ ጋር በሚያስተሳስረው ግንኙነት ውስጥ ጥብቅ የሆነ ቅን ልቦና ሊኖረው እንደሚገባ የሚደነግግ በመሆኑ የንግድ ተላላኪዉ ወይም እንድራሴዉ ከነጋዴ ትዕዛዝ በመዉሰድ በሚሠራቸው በማንኛውም እንቅስቃሴዎች ውስጥ ለለጋዴዉ የተሻለ ጥቅም ሲል በቅንነት ሊሠራ ይገባዋል፡፡ የሚሠሯቸው ድርጊቶች ሁሉ ነጋዴውን ተጠያቂ የሚያደርጉ ስለሆነ በማን አለብኝነት ስሜት ሥራውን መሥራት የለባቸዉም፡፡ የንግድ ተላላኪዉ ወይም እንድራሴዉ የራሱን ጉዳይ ሲሰራ ሊወስደው የሚችለውን ጥንቃቄና ጭንቀት ለነጋዴዉ በሚሠራበት ጊዜ ማድረግ አለበት። ከዚህ በተጨማሪ በፍትሐብሔር ህጉ አንቀጽ 2209(1) እና 2211(1) እንደ ቅደም ተከተላቸዉ የንግድ ተላላኪዉ ወይም እንድራሴዉ ለሚሰራዉ ስራ ታማኝነት/ታማኝ የመሆን ግዴታ/ ታታሪነት /ትጉህ የመሆን ግዴታ ይኖርበታል፡፡

Exit mobile version