Site icon ETHIO12.COM

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማምረት እያቆሙ ነው – “ስለግብዓት እጥረቱ የደረሰኝ መረጃ የለም”የማዕድን ሚኒስቴር

የትኞቹ ግብዓቶች ላይ እጥረት አለባችሁ የሚል ዝርዝር መጠየቁን መልኩን ገልጾ፤ እስካሁን መልስ ባለመገኘቱ ችግሩን አላወቅኩም፤ መፍትሄም መስጠት አልቻልኩም

የማዕድንሚኒስቴር

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በድንጋይ ከሰል ዕጥረትና በተለያዩ የግብዓት ችግሮች የተነሳ ማምረት እያቆሙ መሆኑን የሲሚንቶ አምራቾች ማኀበር አስታወቀ። ለችግሩም መፍትሄ ለመስጠት ማዕድን ሚኒስቴር እንዳልቻለ ማኀበሩ ገልጿል።

የማዕድን ሚኒስቴር በበኩሉ ወደ ማኀበሩንም ሆነ ወደ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ደብዳቤ በመላክ የትኞቹ ግብዓቶች ላይ እጥረት አለባችሁ የሚል ዝርዝር መጠየቁን መልኩን ገልጾ፤ እስካሁን መልስ ባለመገኘቱ ችግሩን አላወቅኩም፤ መፍትሄም መስጠት አልቻልኩም ብሏል።

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በግብዓት ዕጥረትና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተነሳ ማምረት እያቆሙ ነው፤ አንዳንዶችም ችግሩን ተቋቁመው በግማሽ አቅማቸው እያመረቱ ይገኛል ሲሉ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሲሚንቶ አምራቾች ማኀበር አመራር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጸዋል።

ኢስት ሲሚንቶ፣ ኢትዮ ሲሚንቶ፣ ሃበሻ ሲሚንቶ ከችግሩ ተጠቂዎች መካከል መሆናቸውን በመጠቆም፤ ይህን ችግር መፍታት ካልተቻለም እንደ አገር ያለው የሲሚንቶ ምርት ይበልጥ እያሽቆለቆለ መሄዱ እንደማይቀር ተናግረዋል። 

አንዳንዶች የተሻለ አቅም ስላላቸው የግብዓት ክምችት ይዘው ችግሩን ለማለፍ ጥረት እያደረጉ ነው። በተለይም ዳንጎቴ ሲሚንቶ በቂ የግብዓት ክምችት ስለያዘ በጥሩ ሁኔታ እያመረተ ይገኛል። ሙገርን ጨምሮ በርካታ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ግን የድንጋይ ከሰል ጨምሮ የተለያዩ የግብዓት ዕጥረት እየፈተናቸው በመሆኑ የሲሚንቶ ምርት በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ አይደለም ብለዋል። 

ከዚህ ባለፈም የጸጥታ ችግርም በሲሚንቶ ማምረት ስራው አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል። ለአብነት ያህል ኩዩ ሲሚንቶን መውሰድ ቢቻል በጸጥታ ችግር ምክንያት ሥራ አቁሟል። ደርባ ሲሚንቶ በበኩሉ በጸጥታ ምክንያት ዋና ሥራ የሚያከናውን ማሽን ስለወደመበት ሙሉ በሙሉ ሥራ እያከናወነ አይደለም። እነዚህንና የተለያዩ የግብዓትም ችግሮቹን የሚፈታ ተቋም አልተገኘም ሲሉ ገልጸዋል።

 ከዚህ ቀደም ያሉብንን ችግሮች ዘርዝረን ለማዕድን ሚኒስቴር አቅርበን ነበር የሚሉት የሲሚንቶ አምራቾች ማኀበር አመራሩ፤ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ቁጣ ነው የተመለሰለን። ስለሲሚንቶ ሲወራ አንድም ቀን ስብሰባ ውስጥ ያልተገኙ ሰዎች ስለጉዳዩ እየወሰኑ ነው ብለዋል። 

በአንጻሩ ግን ማዕድን ሚኒስቴር እራሱ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ትልቁ ችግር የግብዓት ችግር ነው ብሎ ጥናት አቅርቦ ያውቃል። ነገር ግን ሚኒስቴሩ መፍትሄ መስጠት የሚችሉ ባለሙያዎች የሉትም፤ በአጠቃላይ ማዕድን ሚኒስቴር ለችግሩም መፍትሄ መስጠት አልቻለም ሲሉ በምሬት ተናግረዋል። 

የማዕድን ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር /ወይዘሮ ፍሬሕይወት ፍቃዱ በበኩላቸው፤ ወደ ማኀበሩንና ወደ ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች ደብዳቤ በመላክ የትኞቹ ግብዓቶች ላይ እጥረት አለባችሁ የሚል ዝርዝር መጠይቅ መላካቸውን ገልጸው፤ እስካሁን መልስ ባለመገኘቱ ለችግሩ መፍትሄ መስጠት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

ባለጉዳዩ ይህ ችግር አለብኝ ብሎ ካላቀረበ እንዴት መፍትሄ መስጠት ይቻላል? ያሉት ወይዘሮ ፍሬሕይወት፤ የተጠየቁትን ዝርዝር መጠይቅ መላክ ካልቻሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የግብዓት ችግር መፍታት አንችልም ብለዋል። 

የሲሚንቶ አምራቾችንና የግብዓት አቅራቢዎችን በማወያየት በጋራ እንዲሰሩ የማድረግ ሃሳብ ነበረን፤ ይሁንና የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ችግራቸውን የሚዘረዝር ሪፖርት እንዲያቀርቡ ቢጠየቁም ከአንድ ወር በላይ ምላሽ ባለመገኘቱ ውይይቱንም ማካሄድ አልተቻለም ሲሉ ተናግረዋል። 

በጥቅሉ ግን ለግብዓት እጥረቱ የጸጥታ ችግሮች በተወሰነ መልኩ ተግዳሮች ሆነዋል። ይሁንና ያለውንም ችግር ለመፍታት ያለውን ችግር ቀርቦ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል። 

ማዕድን ሚኒስቴር ትልቁ ሥራው ግብዓት ላይ እጥረት እንዳይኖርና፣ የአካባቢው ሠላም ለፋብሪካው ምቹ እንዲሆንና የአካባቢው ማህበረሰብ ይበልጥ እንዲጠቀም ማድረግ ነው። በመሆኑም የሲሚንቶ አምራቾች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ወደ ሚዲያ ከሚሄዱ ይልቅ ከሚኒስቴሩ ጋር ተቀራርበው ቢሰሩ ይሻላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን የካቲት 2/2014

Exit mobile version