Site icon ETHIO12.COM

ግብይት ሳይኖር የደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ የነበሩ 2 ድርጅቶችና 3 ግለሰቦች ከባድ የቅጣት ዉሳኔ ተላለፈባቸው

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው አባቢን ኮንስትራክሽን እና ማሽነሪ ኪራይ ኃ/የተ/የግ/ማህበር እና ዲን ጀነራል ትሬዲንግ የተባሉ ሁለት ድርጅቶች እና አቶ ቢኒያም አበበ ፣ ደጄኔ ጆቫኒ እና አባይ መኮነን የተባሉ 3 ግለሰቦች ከ2007 ዓ.ም እስከ 2009 ዓ.ም ባሉት የግብር ዘመናት በኮንስትራክሽን ዕቃዎች ሽያጭና በኮንስትራክሽን ማሽነሪ ኪራይ የንግድ ዘርፍ ተመዝግበው፣ አባቢን ኮንስትራክሽን ምንም አይነት ግብይት ሳይኖር 128‚915‚853.75 ብር በሌላ ጊዜ ደግሞ በተመሳሳይ በገዢ ወይም አገልግሎት ተቀባይ ሲጂሲ ኦቨር ሲስ ኮንስትራክሽን ድርጅት ስም ያለ አገልግሎት እና ሽያጭ ተቆርጦ የተዘጋጀ 1‚799‚175 ብር እንዲሁም ዲን ጀነራል ትሬዲንግ 101‚099‚290.39 ብር ግብይት ሳይኖር የደረሰኝ ሽያጭ መፈፀማቸው በኦዲት የተረጋገጠ ሲሆን፤ በልላ በኩል አባቢን ኮንስትራክሽን እና ማሽነሪ ኪራይ ኃ/የተ/የግ/ማህበር እና ዲን ጀነራል ትሬዲንግ በጋራ 24‚203‚255.96 ብር የግብር ስወራ ወንጀል ሲፈፅሙ፤ በተጨማሪም 91‚956‚537 ብር ግብር እንዳለባቸው አሳውቀው ነገር ግን ባለመክፈላቸውና ተከሳሾች 1‚195‚945.54 ብር ምንም አይነት ግብይት ሳይኖር አባይ መኮንን በተባለ ተከሳሽ አማካኝነት ለሁለት የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ደረሰኞችን በ40‚000 ብር እንደሸጡ የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያስረዳል።

ቢኒያም አበበ እና ደጀኔ ጆቫኒ የተባሉት ተከሳሾች የድርጅቶቹ ስራ አስኪያጅ ሆነው ሳለ የሚጠበቀብቻውን ግዴታ ባለመወጣት፣ አባይ መኮንን ጨምሮ ሁሉም ተከሳሾች ደረሰኞችን በመስጠት፣ በመርዳት፣ በማበረታታት፣ በማገዝ እና ግብርን አሳውቆ ባለመክፈል፣ የግብር ስወራ ወንጀል በመፈፀም በመንግስትና በህዝብ ላይ ባደረሱት ጉዳት እንደ ወንጀል ተሳትፏቸው በተለያዩ ክሶች በወንጀል ህግ አንቀፅ 34 (1)፣ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀፅ 120(5)፣125(1)(2) ፣128፣132(1)፣ አንቀፅ 138(1) እና የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀፅ 49 እና 56 ላይ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች በመተላለፍ፤በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የኢኮኖሚና የታክስ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል።

ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 9ኛ ወንጀል ችሎት ዐቃቤ ህግ ተከሳሾች ወንጀሉን ስለመፈፀማቸው የሚያስረዱለትን ዝርዝር የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብና በማሰማት በበቂ ሁኔታ ያስረዳና ተከሳሾችም የቀረበባቸውን ክስና ማስረጃ መከላከልና ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት ተከሳሾች እንደተመሰረተባቸው ክስና እንደ ወንጀል ተሳትፏቸው የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

በዚህ መሰረትም አባቢን ኮንስትራክሽን እና ማሽነሪ ኪራይ ኃ/የተ/የግ/ማህበር እና ዲን ጀነራል ትሬዲንግ እያንዳንዳቸው በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፣ ቢኒያም አበበ እና ደጀኔ ጆቫኒ እያንዳንዳቸው በ18 ዓመት ፅኑ እስራትና በብር 1 ሚሊዮን የገንዘብ ቅጣት እንዲሁም አባይ መኮንን የተባለው ተከሳሽ በ9 ዓመት ፅኑ እስራትና በ750 ሺህ ብር እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።

Exit mobile version