Site icon ETHIO12.COM

የአሜሪካ ዜጎች አሁኑኑ ዩክሬንን ለቀው እንዲወጡ ጆ ባይደን አሳሰቡ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ ሩሲያ በማንኛውም ሰአት ጥቃት ልትጀምር እንደምትችል ጠቅሰው፤ በዩክሬን የቀሩ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ሁሉ ባስቸኳይ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ሩሲያ ዩክሬንን ስትወር አሜሪካውያንን ለማዳን ወታደር አንልክም፣ ስለዚህ በፍጥነት ዩክሬንን ለቃችሁ ውጡ ብለዋል ባይደን፡፡

ነገሮች በፍጥነት እየተቀየሩ እደሆነ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ ያ አካባቢ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ቀውጢ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡

ከ 100 ሺህ በላይ ወታደሮችን በዩክሬን ድንበር ያሰፈረችው ሩሲያ ባንድ በኩል በተደጋጋሚ የወረራ እቅድ እንደሌላት እየገለፀች ቢሆንም በሌላ በኩል ከጎረቤት ሀገር ቤላሩስ ጋር ገዘፍ ያለ ወታደራዊ ልምምድ ጀምራለች

ዩክሬን የኔቶ አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ታቁምልኝ አበለዚያ ቀይ መስመሩን አረግጠዋለሁ እያለች ነው፡፡

ለዚህኛ የሩሲያ ጥያቄ የምዕራባውያኑ ምላሽ ቀድሞ ነገር ምን አግብቶሽ የሚል ሆኗል፤ አንዲት ሉአላዊ ሀገር የፈቀደችውን ማህበር የመቀላቀል መብት አላት በሚል፡፡

የኔቶ አባል ሀገራት የምድር ጦርና የባህር ሀይላቸውን ወደ አካባቢው አስጠግተዋል፡፡ ዩክሬንም የ 10 ቀን ያለችውን ልዩ ወታደራዊ ልምምድ ለብቻዋ ጀምራለች፡፡

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ትናንት አውሮፓ ከአስርት አመታት በኋላ ትልቁን የፀጥታና ደህንነት ቀውስ ተጋፍጣለች ብለዋል፡፡

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርም፤ በአለማችን ግዙፍ የጦር ሀይል ካላት ሀገር ጋር ነው ችግር ውስጥ የገባነው ያለ ሲሆን ሁሉም አሜሪካውያን ባስቸኳይ ዩክሬንን ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል፡፡

በጣም በአደገኝነቱ ለየት ስላለ ሁኔታ ነው እየተናገርን ያለነው ያሉት ባይደንም ያ አካባቢ በፍጥነትና ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ቀውጢ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡

ቢቢሲ

ሔኖክ አስራት
የካቲት 04 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version