Site icon ETHIO12.COM

የታዳጊው ወጣት ሰናይ ተግባር – በደባርቅ ።

በደባርቅ ከተማ የሚኖር አንድ ታዳጊ ወጣት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርገው ድጋፍ እና አስተዋጽኦ የብዙ ሠዎችን ቀልብ ስቧል።

ታዳጊ ወጣት ታምራት ቀፀላ ይባላል። ተወልዶ ያደገው በሰሜን ጎንደር ዞን በደባርቅ ከተማ ነው። ዕድሜው 17 ዓመት ሲሆን የ11ኛ ክፍልም ተማሪ ነው። ለቤተሰቦቹ ደግሞ ብቸኛ ልጅ ነው ። እነሱንም የሚያስተዳድረው በሊስትሮ ስራ ነው።

ወጣት ታምራት ቀፀላ ፣ አሸባሪው እና ወራሪው የህውሃት ቡድን ደባርቅን እና ዳባት ወረዳዎችን ቆርጦ በጎንደር በኩል ለማምለጥ ባሰበበት ጊዜ በጭና አካባቢ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ከስንቅ እስከ ተተኳሽ ድረስ በመሸከም ድጋፍ አድርጊያለሁ ብሏል።

ለመውጣት አይደለም ለመመልከት የሚከብዱ ረጃጅም ተራራዎችን ነጭ ላቡን እና ደሙን እያፈሰሰ በመውጣት ጠላት ሲደመስስ በአካል ተገኝቼ አይቻለሁ ሲል ተናግሯል።

ይህን ተግባሩን ከተመለከትኩ ጊዜ ጀምሮ ለእኔ ሲል በምንም በማንም የማይተካውን ህይወቱን ለሚከፍልልኝ ጀግናው ሠራዊታችን ባለኝ ነገር ለመደገፍ ወሰንኩ ይላል ታዳጊ ወጣት ታምራት።

እኔን እና ቤተሰቦቼን የማስተዳድረው በሊስትሮ ስራ ነው ። አቅሜ የሚፈቅደው ደግሞ ለጀግናው ሠራዊታችን ጫማቸውን በነፃ መቀባት ነው። በዚህም በምሰራበት አካባቢ “ለሀገር መከላከያ ሠራዊታችን በነፃ ጫማ እንቀባለን” ብዬ ፅፌ ለሠራዊቱ በነፃ ጫማ እቀባለሁ ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በእየለቱ ከማገኘው ገቢ 15 ከመቶውን በመቀነስ በየወሩ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እደግፋለሁ ። አሁንም ይህን ተግባር አጠናክሬ እቀጥላለሁ ሲል ጨምሮ ተናግሯል።

የደባርቅ ከተማ ነዋሪ አቶ ጌታቸው አሰፋ ስለ ታዳጊው ወጣቱ ታምራት ቀፀላ እንደተናገሩት ፣ ለሠራዊቱ ጫማቸውን በነፃ በመቀባቱ የአካባቢው ነዋሪ የእሱን ሰናይ ተግባር ተመልክተው በቻሉት መንገድ ሁሉ ጀግናውን ሠራዊት እንዲደግፉ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃትን የፈጠረ ጀግና ወጣት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሠራዊታችን ለሀገር እና ለህዝብ ጥቅም ሲል በሚደረግ የህልውና ትግል ውስጥ ህይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ዛሬም ነገም አያፈገፍግም። የህዝባችን የተባበረ ክንድ ከጎናችን እስካለ ድረስ ደግሞ የድል ባለቤት የመሆናችን ጉዳይ አያጠራጥርም።

ክብር ለደጀኑ ህዝባችን ኢትዮጵያ አሸንፋለች።

ፍፁም ከተማ ( ከግዳጅ ቀጣና )
ፎቶግራፍ አከለ አባተ

Exit mobile version