Site icon ETHIO12.COM

ጄኔራል ጻድቃን ገ/ተንሳኤን ጨምሮ 754 ተከሳሾች በሌሉበት እንዲታይ ቀጠሮ ተሰጠ

ጄኔራል ታደሰ ወረደ እና ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ገ/ተንሳኤን ጨምሮ በ74 ተከሳሾች ላይ የተመሰረተውን የዐቃቤ ሕግ ክስ ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

በእነ ጄኔራል ታደሰ ወረደ የክስ መዝገብ የተከሰሱት የህውሐት ወታደራዊ ቡድን አመራርና አባላት ናቸው የተባሉ አጠቃላይ 74 ተከሳሾች ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ 20 ተከሳሾች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።

ተከሳሾቹ ከህውሐት የሽብር ቡድን ተልዕኮ ተቀብለው ወታደራዊ ቡድን በማደራጀት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ በፌደራል ፖሊስ እንዲሁም በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ ጥቃት ማድረስ ወንጀል በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ክስ አንደተመሰረተባቸው ይታወቃል ።

ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ-ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የቀረቡት ኮ/ል ገ/መስቀል ገ/ኪዳን እና ኮ/ል ዶ/ር አለምብርሃንን ጨምሮ 19 ተከሳሾች ሲሆኑ አንድ ተከሳሽ በህመም ምክንያት ከማረሚያ ቤት አለመቅረቡ ተገልጧል።

ፍርድ ቤቱ በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ከ1ኛ እሰከ 47ኛ ፣ 49ኛ፣ 50ኛ እና ከ52ኛ እስከ 56ኛ ያሉ በአጠቃላይ 54 ተከሳሾችን ፖሊስ ከመከላከያ ጋር በመተባበር እንዲያቀርባቸው በተሰጠው ተደጋጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮ አለመቅረባቸውን ተከትሎ ፖሊስ ያላቀረበበትን ምክንያት እንዲያስረዳ ታዞ ነበር። ይህን ትዕዛዝ ተከትሎ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተከሳሾቹ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንደነበሩ በመጥቀስ የትግራይ ልዩ ሀይል አባል በመሆን በጦርነቱ በመሳተፍ እና በመምራት ላይ የነበሩ መሆናቸውን ማብራራቱ የሚታወስ ነው ።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሾቹ የተከሰሱበት የወንጀል ህግ ድንጋጌ ከ12 አመት በላይ የሚያስቀጣ መሆኑን አብራርቶ በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ተደርጎ የማይቀርቡ ከሆነ ያልቀረቡ ተከሳሾች ጉዳይ በሌሉበት እንዲቀጥል እንዲታዘዝ ፍርድ ቤቱን በመጠየቁ ፍርድ ቤቱ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርአት ህጉ መሰረት ያልተያዙ 54 ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ በመስጠቱ የኢትዮጲያ ፕሬስ ድርጅትን የጋዜጣ ጥሪ ውጤት ለመጠባበቅ ለየካቲት 8 ቀን 2014 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል ።

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በዛሬው የካቲት 08/2014 ዓ.ም በያዘው ቀጠሮ በቁጥጥር ስር ያልዋሉ 54 ተከሳሾች በጥር 16 /2014 ዓ.ም በታተመው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገፅ 21 ላይ የጋዜጣ ጥሪ የተደረገላቸው መሆኑን አረጋግጧል ።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በቁጥጥር ስር ያልዋሉት 54ቱ ተከሳሾች በችሎት ባለመቅረባቸው መዝገቡ በሌሉበት እንዲታይ በመወሰን የዐቃቤ ሕግን ክስ ለመስማት ለየካቲት 22 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።

– Source attorney general Fb

Exit mobile version