Site icon ETHIO12.COM

ጫት በእንጀራ ጠቅልሎ ከሀገር ሊወጣ ሲሞክር የተያዘው ሰዊድናዊ በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ተወሰነበት

ሚ/ር አብዱላሂ አብዲ የተባለው ሰዊድናዊ ዜግነት ያለው ተከሳሹ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀፅ 168(1) በአዋጅ ቁጥር 1160/2011 አንቀፅ 44 እንደተሸሻለው እና የአየር መንገድ ተጓዦች ከኢትዮጵያ ይዘው መውጣት የሚችሉትን የተለያየ የግብርና ምርቶችና የፋብሪካ ውጤቶች ለመወሰን የወጣውን መመርያ ቁጥር 008/2007 በመተላለፍ መጋቢት 10 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 3:00 ሰዓት ሲሆን ከአዲስ አበባ ወደ ስዊድን ሀገር ለመጓዝ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል መንገደኞች ማስተናገጃ ሲደርስ ዕቃዎች ወደ አውሮፕላን ከመጫናቸው በፊት ባለው የፍተሻ ቦታ ተከሳሽ በያዘው ሻንጣ ላይ በተደረገ የኤክስሬይ ፍተሻ ሥልጣን ባለው አካል በተሰጠ ፍቃድ ካልሆነ በስተቀር ከሀገር እንዳይወጣ ገደብ የተደረገበትን ክብደቱ 17 ኪሎ ግራም የሚመዝን እርጥብ ጫት በአንጀራ በመጠቅለል ሻንጣ ውስጥ አድርጎ ከሃገር ሊወጣ ሲሞክር በመያዙ በፈፀመው የኮንትሮባንድ ወንጀል በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶበታል ።

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ እና ታክስ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ ላይ ባቀረበው በዚህ ክስ ላይ የተጠቀሰው ወንጀል በመፈጸሙ ምክንያት መንግስት ማግኘት የነበረበትን የውጭ ምንዛሬ 595 USD (አምስት መቶ ዘጠና አምስት ዶላር) በዕለቱ የነበረው የውጭ ምንዛሬ 24‚663‚78( ሃያ አራት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ሶስት ብር ከሰባ ስምንት ሳንቲም ) እንዲያጣ አድርጎታል ይላል፡፡

ተከሳሹ በፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምደብ ወንጀል ችሎት ቀርቦ በተመሰረተበት ክስ ላይ የእምነት ክህደት ቃሉን ተጠይቆ “በዐቃቤ ህግ በተመሰረተብኝ ክስ ጥፋተኛ ነኝ በዚህም የኢትዮጵያን ህዘብና መንግስት ይቅርታ እጠይቃለሁ” ሲል በአስተርጓሚ ታግዞ ለችሎቱ የእምነት ቃሉን ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ የሰጠውን የእምነት ቃል መሰረት በማድረግ ተጨማሪ የዐቃቤ ህግ ዝርዝር የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች መስማትና ማየት ሳያስፈልገው የጥፋተኝነት ውሳኔ በመስጠት እና የቅጣት ማቅለያዎችን በመያዝ በ4 ዓመት እስራትና በ35 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ወስኖበታል ።

Exit mobile version