Site icon ETHIO12.COM

ʺለአርበኞች መሞትን ማን አስተማራቸው፣አቡነ ጴጥሮስ ነው ባርከው የሰጧቸው”

ባሕር ዳር: የካቲት 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሞትን ናቁት፣ የግፍ ግድያን ረሱት፣ ለሀገር ክብር ሲሉ መራራ ነገርን ተቀበሉት፡፡ ድሮም ኢትዮጵያዊ ተዋርዶ ከመኖር፣ ተከብሮ መሞትን ይመርጣል፡፡ ክብር ለኢትዮጵያዊ ከምንም በላይ ናት፡፡ በምንም አትለካም፣ በምንም አትተካም፡፡ ክብር የሚተካው በክብር ፣ ፍቅርም የሚተካው በፍቅር ብቻ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ኢትዮጵያዊ ይነግሳል፣ ያዝዛል፣ ኢትዮጵያውያንንም ይመራል እንጂ በዓድ ኢትዮጵያውያንን አይመራም፣ አያዝዝም፡፡ ማድረግ አይደለም ማሰብ አይፈቀድም፡፡
ድንበር አትጣሱ፣ ሃይማኖት አታርክሱ፣ አልደረስንባችሁም አትድረሱብን ያሉት ሁሉ መከራው በዛባቸው፣ ችግሩ ጸናባቸው፣ ጦር ተመዘዘባቸው፣ ሠራዊት ዘመተባቸው፣ እነርሱም ለክብርና ለሀገር ፍቅር ሲሉ ተቆጥተው ተነሱ፡፡ ኢትዮጵያዊ በክብሩና በሀገሩ እንደማይደራደር እያወቁ ጦር አዘመቱበት፡፡ እንግጠምህ አሉት፡፡

ለዘመናት የገነባችው ሥሟ በዓድዋ ተራራ ላይ የፈረሰባት፣ በእኩለ ቀን የጨለመባት፣ ኃያልነት የራቃት፣ ክብሯ የወደቀባት፣ ጎዳናዎቿ ጭር ያሉባት፣ ልጆቿ ከኢትዮጵያ አፈር ጋር ላይነሱ የተቀላቀሉባት፣ በዓለም ፊት የተዋረደችው፣ የክብር ልብሷን አውልቃ የሄደችው፣ ለኢትዮጵያውያን ጀግኖች የተንበረከከችው፣ እጇንም የሰጠችው ጣልያን ሌላ እድል ትሞክር ዘንድ አስባለች፡፡
የድል ዜና ለመስማት የቋመጡት የጣልያን ሹማምንት፣ መኳንንት፣ መሳፍንት፣ ወይዛዝርትና በሮም አደባባይ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ የሚንጎማለሉ ጎበዛዝት ያልጠበቁት ዱብዳ ከወደ ኢትዮጵያ ደረሳቸው፡፡ ሂዱ በድል ተመለሱ ተብለው የተላኩት፣ በሮም አደባባይ ፎክረው የተነሱት ወታደሮች በኢትዮጵያውያን ጀግኖች እንዳልነበር ኾነዋል ተባሉ፡፡ ያን ጊዜ ሮም በጨለማ ተዋጠች፣ በጥቁር ልብስ ተጠቀለለች፣ አንገቷን ደፋች፣ በዓለም ፊት አፈረች፡፡ በተሸናፊዎች መዝገብ ሥር ደመቅ ብሎ በተጻፈ ብዕር ሠፈረች፡፡ ሹማምንቱ ወኔ ራቃቸው፣ መላ ጠፋባቸው፡፡ ሀዘን ከበባቸው፡፡

ዓድዋ በብርሃን ተመላች፣ የማትጠልቀው ፀሐይ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር በራች፣ ወደ ጥቁር ምድር አፍሪካም ሰፋች፣ ከፍ ብላም አበራች፡፡ መልካሙን መንገድም አመላከተች፣ ጠረገች፡፡
በዚያ ዘመን በዓድዋ ተራራ ላይ የማይረሳ ሽንፈት የቀመሱት ጣልያናውያን ለዳግም ወረራ ይዘጋጁ ነበር፡፡

የዓድዋው ጀግና እምዬ ምኒልክ፣ ብልኋ እመቤት ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ደማቅ ታሪክ ጽፈው አልፈዋል፡፡ ስማቸውን ግን እንዳይጠፋ አድርገው አስቀምጠዋል፡፡ በአስፈሪው ዙፋን ላይ የዓድዋው የጦር አበጋዝ ቆራጡ ተዋጊ የራስ መኮንን ልጅ ተፈሪ መኮንን ሞዓ ፡ አንበሣ ፡ ዘእም ነገደ ፡ ይሁዳ ፡ ቀዳሚ ኃይለ ሥላሴ ሥዩመ ፡ እግዚአብሔር ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ተብለው ነግሠዋል፡፡ የሽንፈት ብርድ ያሰቃያት፣ የጨለማ ካባ የከበባት፣ በቀን የጨለመባት የሮም አደባባይ ለዳግም ወረራ የተነሳው ሠራዊት ፎከረባት፡፡ በዓድዋ ተራራ ላይ ጥሎት የሄደውን ሥሙን አንስቶ እንደሚመለስ ቃል ገባ፡፡ ባሕር ሰንጥቆ የብስ አቋርጦ የኢትዮጵያን መሬት ረገጠ፡፡

የኢትዮጵያ ጀግኖችም ጦር ሰብቀው ተነሱ፡፡ ጠላት መጣበት ወደ ተባለው አቅጣጫ ገሰገሱ፡፡ የጦርነቱ ጊዜ ደረሰ፡፡ ጀግኖች የገባውን ጠላት ሰቅዘው ያዙት፡፡ ቀናት አለፉ፡፡ ወራት ተተካኩ፡፡ ለኢትዮጵያ ክብርና ፍቅር ሲባል ደም ፈሰሰ፣ አጥንት ተከሰከሰ፡፡ በዚሕ የጣልያን ወረራ ዘመን ስማቸው ከፍ ብሎ የሚነሳ አንድ ታላቅ አባት አሉ፡፡ ቅዱሱ ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ፡፡ እኒህ ታላቅ አባት በ1921 ዓ.ም በእስክንድሪያ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን የጵጵስና ማዕረግን ከተቀበሉ አራት ቅዱሳን ጳጳሳት መካከል አንደኛው ናቸው፡፡
እኒህ መልካም አባት ጣልያን በኢትዮጵያ ላይ በተነሳች ጊዜ እርሳቸውም በቁጣ ተነሱ፡፡ የተቀደሰችውን ሀገር ባዕድ አያረክሳትም፣ ጠላት አይደፍራትም አሉ፡፡

ጦርነቱ አይሏል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ለዓለም አቤት ሊሉ ወደ ውጭ ወጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞች ግን በዱር በገደል መዋደቁን ቀጥለውበታል፡፡ ከአንደኛው ጎራ ወደ ሌላኛው ጎራ እየተሸጋገሩ፣ ከአንደኛው አውራጃ ወደ ሌላኘው አውራጃ እያቀኑ የጠላትን ሠራዊት ረፍት ነሱት፡፡ ግንባሩን እየመቱ በየጥሻው ጣሉት፡፡ በዚህ ወቅት ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያን ጀግኖች አይዟችሁ ይሏቸው ነበር፡፡
ኢትዮጵያውያን በግፍ ሳይሆን ለግፍ ነበርና የዘመቱት አይዟችሁ አሏቸው፡፡ እኒህ አባት ከሠራዊቱ ጋር በሰሜን ኢትዮጵያ ዘምተው ሠራዊቱን አበረታትተዋል፣ አባታዊ ቡራኬ አድርሰዋል፤ እውነት የያዘችው ኢትዮጵያ ድል ታደርግ ዘንድ በጸሎታቸው ታግለዋል፡፡ ጦርነቱ ቀጠለ፡፡ እሳቸውም በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተቀመጡ፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በገዳመ ደብረ ሊባኖስ ኾነው አርበኞቹን አበረታትተዋል፡፡ አንቅተዋል፡፡ በቆራጥነት እንዲነሳ አድርገዋል፡፡
የታላቁን አባት ስብከት የሚሰሙ ሁሉ አርበኞችን እየተቀላቀሉ ጠላትን መውጫ መግቢያ አሳጡት፡፡ የጣልያን የጦር አዛዦችም በእኒህ አባት ላይ ቂም ቋጠሩ፡፡ በጣልያን ላይ ያላቸውን አቋም እንዲቀይሩ የሚለምናቸው በዛ፡፡ እርሷቸው ግን በሀገር ጉዳይ አይደረግም አሉ፡፡ አርበኞች ጥቃታቸውን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡ ጣልያኖች እኒህን አባት ይዘው መግደል እንዳለባቸው አመኑ፡፡ እርሳቸው ሲሞቱ የሚነሳውን ያላወቁ፡፡

አቡነ ጴጥሮስ በጣልያን ወታደሮች ተያዙ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ የኢትጵያና የኢጣልያ ጦርነት በሚለው መጽሐፋቸው የኮሪየር ዴላ ሴራ ጋዜጠኛ የነበረው ፓጃሊ ድእርዮ በሚል ርእስ ያሳተመውን መጽሐፍ ዋቢ አድርገው ሲገልጡ ʺእ. ኢ. አ ሐምሌ 30 በጳጳሱ ላይ የተቋቋመው ችሎት ሕዝብ በተሰበሰበበት እንዲገደሉ ፈረደ፡፡ ይህ ሲሰማ በከተማው ሕዝብ ዘንድ ሽብር ፈጠረ፡፡ ጉዳዩም በጋዜጣ እንዳይወጣ ፋሽሽቶች ታላቅ ቁጥጥር አደረጉ፡፡ ለእኛም ትዕዛዝ ተሰጠን፡፡ ማንኛውም ጋዜጠኛ አቡኑ ተገደሉ ብሎ ወደ ኢጣልያ ሀገር ቴሌግራም እንዳያደርግ ክልክል ነው፡፡ አቡኑ ታሰሩ ብላችሁ ግን ዜናውን ማስተላለፍ ትችላላችሁ አሉን ” ብለዋል፡፡

በአቡኑ ላይ የተወሰነው ውሳኔ ሲሳማ ብዙዎችን አስቆጣ፡፡ ʺየሞት ፍርድ በተፈረደባቸው ጊዜ በጸጥታ አዳመጡ፡፡ በቀኝ እጃቸው በሰማያዊ ጨርቅ የተጠቀለለ መስቀል ይዘዋል፡፡ የሞት ፍርዱ ከተፈረደ በኋላ ጣልያኖቹ የመግደያውን ቦታ ለማዘጋጀት ወደገበያ ሄዱ፡፡ የመግደያው ቦታ ተዘጋጅቶ አቡነ ጴጥሮስ ተወሰዱ፡፡ ፊታቸውንም ወደ ተሰበሰበው ሕዝብ አድርገው ቆሙ፡፡
“በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚከበሩትን፣ የሚወደዱትን፣ መሪ፣ አሻጋሪ የተባሉትን ሊገድሏቸው ተቻኮሉ፡፡ ተፋጠኑ፡፡ የእውነት አባት፣ የእውነት መምህር፣ የእውነት መሪው አቡነ ጴጥሮስ ሞትን ናቁት፡፡ ስለ እውነት መሞት የሚያስገኘውን ዋጋ አስቀድመው ያውቁታልና በገዳዮቻቸው ፊት በኩራት ቆሙ፡፡ ገዳዮቻቸው ገድለው ይሸነፋሉ፡፡ እርሳቸው ግን ሞተው ያሸንፋሉና፡፡

ዜና ቤተክርስተያን ጋዜጣን ዋቢ አድርገው ጳውሎስ ኞኞ ሲገልጹ ʺ ከሚገደሉበት ሥፍራ ሲደርሱ አራቱን ማዕዘን በመስቀላቸው ባረኩ፡፡ በሕዝቡም ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፡፡ ፋሽሽቶች የሀገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢሏቸው እውነት አይምሰላችሁ፡፡ ሽፍታ ማለት ያለ ሀገሩ መጥቶ የሰውን ሀገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ የቆመው አረመኔው የኢጣልያ ፋሽሽት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሱ እንዳይገዛ ውጉዝ ነው፡፡ የኢትዮጵያም ምድር እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን” ቅዱሱ አባት በጠላቶቻቸው መሃል ሆነው ስለ እውነት የእውነት ተናገሩ፡፡ የጠላትን እርኩሰት ፊት ለፊት ተናገሩ፡፡ የአቡኑን ቃል ሁሉም በልቡ ላይ መዘገበ፡፡ የኢትዮጵያ ምድርም ሰማች፣ ታዘበች፣ በምድሯ ጠላትን ላለመቀበል ውግዘቱን ተቀበለች፡፡

ʺአቡነ ጴጥሮስ ሰዓታቸውን አውጥተው አዩ፡፡ ወዲያውም ከአጠገባቸው ያለውን ኢጣሊያ ለመቀመጥ እንዲፈቅድላቸው ጠየቁት፡፡ ቀና ብለው ሰገነት ላይ ወደተቀመጥነው ጋዜጠኞችና መኳንንት አይተው የመቀመጥ ጥያቄያቸውን ትተው ቀጥ ብለው ቆሙ፡፡ ከፊታቸው ለቆሙት ገዳዮቻቸው ተመቻቹላቸው፡፡ ከቦታው ሲደርሱ አንድ አስተርጓሚ ተጠግቶ ዓይንዎ እንዲሸፈን ይፈልጋሉን? አላቸው፡፡ የእናንተ ጉዳይ ነው፣ እንደወደዳችሁና እንደፈለጋችሁ አድርጉ” አሉ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ታላቁን አደራቸውን ጥለው፣ የማይሻረውን ቃላቸውን አስቀምጠው ምድርን ሊሰናበቷት ተቃርበዋል፡፡ ገዳዮቹ ቅዱሱን አባት ለመግደል ጓጉተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ታላቅ ሰው ሊወድቅ፣ ጥላው ሊታጣ ነው፡፡

ʺከዚያ በኋላ አቡነ ጴጥሮስ ፊታቸውን ወደ ግድግዳው እንዲያዞሩ ተደረገ፡፡ እሳቸውን ቀድሞ በመግደል ክብር የሚፈልጉት ስምንት ካራሚኜሮች ከጴጥሮስ 20 ርምጃ ያህል ርቀው በርከክ አሉ፡፡ በአስተኳሹ ትዕዛዝም ተኮሱ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ጀርባቸው በጥይት ተበሳሳና ከመሬት ላይ ወደቁ፡፡ “ታለቁ አባት በስጋ ላይታዩ ምድርን በግፈኞች እጅ ተሰናበቷት፡፡ አባታቸውን በመግደል ልጆቹን ለመበተን የፈለጉት ጣልያኖች የበለጠ አስቆጧቸው፡፡ አርበኞች በእልህና በብስጭት ተነሱ፡፡ የአባታቸውን ቃል ይፈጽሙ ዘንድ ሳያሸንፉ ላይቀመጡ አምርረው ዱር ቤቴ አሉ፡፡

ʺለአርበኞች መሞትን ማን አስተማራቸው
አቡነ ጴጥሮስ ነው ባርከው የሰጧቸው” እንደተባለ የኢትዮጵያ አርበኞች የአቡኑን መሞት ሲሰሙ የበለጠ በረቱ፡፡ ሞትን ናቁ፡፡ ለክብር ታገሉ፡፡ ለእናት ሀገር መሰዋትን ፈለጉ፡፡ ሕዝቡም ተቆጣ፡፡ አቡኑን ገድለን ሰላም እናገኛለን ያለው ወራሪ የበለጠ እሳት ውስጥ ገባ፡፡ አርበኞቹ ቀን እና ሌሊት ሳያቋርጡ፣ የተመቻቸ ኑሮ ባልነበረበት፣ ከባድ መሳሪያ ባልተጫነበት ከጠላት ጋር ተናነቁ፡፡
ጠላትን ድል አድርገው ሀገር ነጻ አወጡ፡፡ ለኢትዮጵያ የተፈጠረው ማሸነፍ ብቻ ነው፡፡ በዓድዋ ተራራ ላይ የወደቀው የጣልያን ስም ዳግም በኢትዮጵያ ምድር ወደቀ፡፡ የኢትዮጵያውያን ጀግንነት ደግሞ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ይነገር ጀመር፡፡ ስማቸው ከፍ አለ፣ ኢትዮጵያም ከፍ አለች፡፡ አርንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ ሠንደቅ ከፍ ብላ ተውለበለበች፡፡ ክብር ሞተው ላከበሯት፡፡

በታርቆ ክንዴ – አሚኮ

Exit mobile version