Site icon ETHIO12.COM

‹‹አካሌ››

(የግል ሥሜት ቅልቅል ዳሰሳ)

ወርሃ መስከረም፣ ሺ ዘጠኝ መቶ ሰባ ስድስት ዓመተ ምሕረት፣ የኤፍሬም ታምሩ ‹‹ነዪልኝ›› አልበም ለሰሚ ጆሮ በቃ። በዚህ አልበም ውስጥ ከተካተቱ ዘፈኖች መካከል ለ‹‹አካሌ›› ልዩ ፍቅር አለኝ፤ ዘፈኑ፡- ግጥምና ዜማው ልዩ ናቸው፤ ሙዚቃው፡- ዓይነቱ (አንቺ ሆዬ)፣ አሬንጅሜንቱ፣ ቅንብሩ እና የኤፍሬም ድምጽ ልከኛ ናቸው። አልበሙ፣ ብሎም ዘፈኑ በአሥር ዓመት ታላቆቼ ናቸው፤ አልበሙ መስከረም 1976 ዓ.ም. ሲለቀቅ፣ እኔ ደግሞ ኅዳር 1986 ዓ.ም. ተወለድኩ።

‹‹አካሌ›› የአበበ መለሠ ዜማ እና የይልማ ገ/አብ ግጥም ሙዚቃ ነው። ሮሃ ባንድ (ሰላም ሥየም፡- ሊድ ጊታር፣ ዳዊት ይፍሩ፡- ኪ-ቦርድ፣ ጂኦቫኒ ሪኮ፡- ቤዝ ጊታር) አቀናብረውታል። በዕድሜ ከፍ ስል፣ እዚያ ላይ ለተሳለች ኢትዮጵያዊት ቆንጆ እና ጠንካራ ሴት የሕግ ሁሉ ፍጻሜ የሆነው ፍቅር አድሮብኛል።

በሙዚቃ ውስጥ ለምትሳል ሴትም ትሁን አገር በልባችን ውስጥ የረቀቀ ሥፍራ ይኖረናል፤ አገሬን የተዋወኳት ተዟዙሬ ጎብኝቻት አይደለም። ከማውቃቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ካፋ (ትውልድና ዕድገት)፣ ጅማ፣ አዲሳባ፣ ሚዛን፣ ጉራጌ፣ ዲላ፣ ሰላሌ፣ አምቦ፣ ደብረብርሃን… ብቻ ተጠቃሾች ናቸው። ነገር ግን ከዚህ የተረፉትን የማውቃቸው በሙዚቃና በመጻሕፍ ነው፤ የአገር ፍቅር ያደረብኝም ልዩ ጥቅም አግኝቼ ሳይሆን መጻሕፍት በማንበብና ሙዚቃ በማድመጥ ነው።

…..አሁኔ ‹‹አካሌ›› ነው…..

……ውብ እና ተናፋቂ እንስት እዚያ ውስጥ ትታየኛለች። ለአመል ቢጤ እንኳን የምትግደረደር….

‹‹….አካሌ፣ ሸግዬ – ነዪ፣

በምትወጃት እናት፣ ሰው ጠራኝ ሳትዪ፣….›› የተባለላት።

በዘፈኑ ውስጥ ያለ ተብከንካኝ አፍቃሪ ማፍቀሩን ከመግለጹ በፊት ሠላምታ ይሰድላታል፤ ኳስ በመሬት ዓይነት ስልታዊ ማዳከም….

‹‹….እንደምን አድረሻል፣ አንቺ አመለ ኩሩ፣

አማላጅ ጠፋልሽ፣ ባገር በመንደሩ፣….›› ሲል።

ለጥቆ ደግሞ በልቡ ምን ያህል ሥፍራ እንዳላት በሚያባቡ ስንኞች ይተርካል፤ በውስጡ መግዘፏን፣ አለያም ስለ-እሷ ሲብከነከን እንደሚውል እንደዚህ…..

‹‹….የማብሰልሰል ሚስጢር፣ የሃሳብ ሹክሹክታ፣

መወያየት ሆኖአል፣ ገጥሞ ከትዝታ፣….›› ሲል እንሰማዋለን።

መልሶ ደግሞ መከታው ያደረጋት እንስት ትሆናለች፤ እናም….

‹‹…የትከሻዬ ጌጥ፣ የጫንቃዬ መስፋት…

ያዕምሮዬ ድባት፣ ሸክሜ ትዝታ…›› ይላታል።

አፍቃሪው ንፉግ አይደለም፤ ፍቅር መስጠት መሆኑን ልብ ብሏል፤ ሌላው እጅ መስጠቱ ጸጋ እንጂ ቀጋ እንዳይደለ ገብቶታል። በሸጋ አመልና በድንቅ ውበቷ ልቡን ገዝታዋለች፤ አይገዳደራትም። ለዚያ ነው….

‹‹…ተራመጅ በልቤ፣ በለመድሺው መንገድ፣

ያንቺማ ትዝታ፣ በሰው አይታገድ፣…›› የሚላት።

መልሶ ይብከነከናል፤ ናፍቆት እያደር ይጣምነዋል፤ እናም ገሃድ አውጥቶ በሸንጎ መዳኘትን ይሻል። ጥቃቱን እንደዚህ በማለት ይለፍፋል….

‹‹….ቢፈርደኝ ምን አለ፣ ዳኛው ተሰይሞ፣

ቂመኛው ልቧማ፣ አጠቃኝ አድሞ፣….››

ፍቅር ይቅርታ መሆኑ የገባው አፍቃሪ ነው፤ እናም ጣመነኝ ብሎ አያቄምባትም። ይልቅዬ በፍቅረኞች መካከል ዳኝነት የልብ እንደማያደርስና ከእርሷ ውጭ ሕማሙን የሚፈውስ ሰው እንደሌለ ስለተረዳ ፋይሉ ተዘግቶ እርሱ ዘንድ እንድትመጣ ይጋብዛታል፤ እንደዚህ….

‹‹….ድረሽ ልቀበልሽ፣ እጆቼን ዘርግቼ፣

አልካስ በዳኛ፣ አንቺን ረትቼ፣….›› በማለት።

ፍቅር አብዛኛውን ጊዜ የመተሳሰብ፣ የመዋደድ እና የመላመድ ውጤት ነውና፤ እንኳን እርሱ ቀርቶ የለመዳት ቤት መናፈቁን እንሰማለን….

‹‹….የለሽ ካጠገቤ፣ ኃይሎ ትዝታ፣

‘ኔም አስብሽ ጀመር፣ ምሰሶና ዋልታ፣….››

አፍቃሪው ጮሌ ነው፤ ይወራረድላችኋል፡፡ እናም በአካል ተገኝታ ከተዘፈቀበት የትዝታ ማጥ እንድታወጣው በውስጡ ስለቀመረ በመምጣቷ ውርርዱን እንዲያሸንፍ ይማጸናል፤ በውርርድ ሰበብ ሊያገኛት እንደማለት ዓይነት ብልጠት….

‹‹…..ውበትሽ ተወርቶ፣ ሙግት ተነስቶበት፣

ተወራርጃለሁ – እንዳልረታበት፣…..›› ይልላችኋል፡፡

በውርርዱ ወቅት አፍቃሪው ባቀረበላቸው ማብራሪያ መተማመን ላይ ያልደረሱ ተቃራኒ ቁማርተኞችን ለማሳመን ምስክር ጠርቶ ከሚንከራተት ራሷ በአካል ብትገኝ ምን ያህል ውብ እንደሆነች ይገባቸዋል ብሎ ያምናል፤ የሚረታው ደግሞ ትዝታውንና ተጻራሪዎቹን ነው፡፡ ለዚያ ነው….

‹‹….ይቅር ለምስክር፣ እርቄ መሄዴ፣

ባካል ድረሺና፣ ልርታልሽ መወደዴ፣…..›› የተሰኘው፡፡

ስጠቀልል፣ ‹‹አካሌ›› አመለ ሸጋ እና ተናፋቂ እንስትን የተዋወቅንበት ዘፈን ነው፡፡ ያ-ነኹላላ አፍቃሪ፣ ውበቷ ልቡን ሞልቶት ለውርርድ ሲበቃ እናስተውላለን፡፡ ይህቺን የመሰልሽ ሴት ከወዴት አለሽ!?

ሠላም ሁኑ!!

(በ፡- ዮናስ ታምሩ) Book for all

Exit mobile version