ETHIO12.COM

የአሸባሪው ግፍ በአፋር …

አፋር አብአላ የወይዘሮ አዋሽ ዱሮ መንደር በጁንታው ከባድ መሳሪያ ሲደበድብ ከተቃጠሉት ቤቶች አንዱ ታዳጊዎቹ የነበሩበት የወይዘሮዋ ቤት ነው።

ሁለቱ ታዳጊዎች ቤት ውስጥ እንዳሉ የትህነግ ከባድ መሳሪያ ቤቱ ላይ አርፎ ቤቱ ነደደ። ታዳጊዎቹም ከቃጠሎው አልተረፉም።

አሸባሪው ትህነግ በአማራና አፋር ሕዝብ ላይ ያደረሰው ግፍና በደል ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም።

በተለይ ቡድኑ በሚሌ ግንባር የኢትዮ- ጅቡቲን መንገድ በመቁረጥ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጫና ለማሳደር በተደጋጋሚ ሙከራ አድርጓል፡፡ በዚህም ሰላማዊ ዜጎችን በከባድ መሳሪያ ጨፍጭፏል፤ ንብረት አውድሟል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችንም አፈናቅሏል፡፡

ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎች ውስጥ አሁንም ህክምናቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙም አሉ፡፡

እኛም በአሸባሪው ሕወሓት የጭካኔ በትር ያረፈባቸው ዜጎች ለማናገር በዱብቲ ጠቅላላ ሆስፒታል በተገኘንበት ወቅት ህክምናቸውን በመከታተል ላይ ከሚገኙ ሁለት ወንድማማች ታዳጊዎች ላይ ዓይናችን አረፈ፡፡

ሁለቱ ወንድማማቾች ጣሂር ደርሳ እና ኑር ደርሳ ይባላሉ፡፡ ዕድሜያቸው የስምንትና የ10 ዓመት የሆኑት ወንድማቾች የአብአላ ወረዳ ነዋሪዎች ናቸው፡፡

አሸባሪው ሕወሓት በአፋር ክልል በዳግም ወረራ ጦርነት በከፈተበት ወቅት ቤታቸው በከባድ መሳርያ በመመታቱ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡

የ8 ዓመቱ ጣሂር ሰውነቱ ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል፡፡ ህክምናቸውን የሚከታተሉበት ጠባብ ክፍል ውስጥ እነሱን ጨምሮ አራት ታካሚዎች አሉ፡፡

ይህ ደግሞ ከዱብቲ ሙቀት ጋር ተዳምሮ ሁኔታውን እጅግ ዘግናኝ አድርጎታል፡፡ ታዳጊው የቆሰለውን ሰውነቱን ለመንካት ስለሚፈራና ህመም ስላለው እናቱን በምልክት እየጠራ እንድታክለት ይነግራታል፡፡ በዚያ ቦታ ይህን ትእይንት መመልከት በራሱ ከባድ በመሆኑ አብዛኛው አዲስ ጠያቂ እንባውን ሳያፈስ አይወጣም፡፡

ታላቅ ወንድሙ ኑር ደርሳ ደግሞ ቃጠሎ የደረሰበት እግሩ ላይ ነው፡፡ ምንም እንኳ እሱ ከጣሂር አንጻር የደረሰበት ጉዳት ቀለል ያለ ቢሆንም ከባድ ህመም የሚሰማው ስለመሆኑ ከሚያሰማው ድምጽ መገመት ይቻላል፡፡

አሸባሪው ሕወሓት ያለምንም ጥፋታቸው እነዚህን ህፃናት ገና በዚህ ለጋ እድሜያቸው ብዙ መከራና ፈተና አሳይቷቸዋል፡፡ ጉዳታቸውን ለተመለከተ በዚህ ለጋ ዕድሜያቸው ምን በድለው ነው እንዲህ የሚሰቃዩት የሚል ውስጣዊ የህሊና ጥያቄን ያጭራል፡፡

የጣሂርና የኑር እናት ወይዘሮ አዋሽ ዱሮ ስምንት ልጆች አሏቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት አሸባሪው ሕወሓት አብአላ በደረሰበት ወቅት ቤታቸው በከባድ መሳሪያ በመመታቱ የእሳት ቃጠሎ ተነሳ፡፡ በወቅቱ ልጆቹ ቤት ውስጥ ስለነበሩ በእሳት ሊቃጠሉ ችለዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ባገኘው ሰውና እንስሳት ላይ ሁሉ ከባድ መሳሪያ ስለሚተኩስ በርካታ ሰዎች ሞተዋል፤ በርካቶችም ቆስለዋል ይላሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ይተዳደሩባቸው የነበሩ 30 ላሞች፣ 25 ፍየሎች እና ስምንት ግመሎች በአሸባሪው ሕወሓት ተወስዶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ቡድን ቤተሰባቸውንም ሆነ መላ የአካባቢያቸውን ሕዝብ ለከፍተኛ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መዳረጉን ይገልጻሉ፡፡

ወይዘሮ አዋሽ ለልጆቻቸው የሚሰጠው ሕክምና በቂ ነው የሚል እምነት የላቸውም፡፡ እኛም ባገኘናቸው ወቅት ይህን ስሜት ለመገንዘብ ችለናል፡፡ ጋዜጠኞች ነን ፤ ስለጉዳዩ እንዲነግሩን ነው የሚል ጥያቄ ስንሰነዝርም ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ምክንያቱም እስካሁን ለሚዲያም ሂነ ለሊሎች አካላት ብዙ ጊዜ ብናገርም በቂ ህክምና ልጆቼ አላገኙም ይላሉ።

እኛም የልጆቹን ህክምና በመከታተል ላይ ለሚገኙት ዶክተር አስፈራው ስሜነህ የልጆቹ የጉዳት መጠን ምን ያህል ነው የሚል ጥያቄ አነሳን፡፡ ዶክተር አስፈራው እንደሚገልጹት፤ በተለይ ጣሂር ደርሳ ሰውነቱ ሙሉ ለሙሉ የተቃጠለ በመሆኑ የጉዳቱ መጠን ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ልጆቹ ጉዳቱ የደረሰባቸው በቤት ውስጥ እያሉ በመሆኑ በጭስ የመታፈን አደጋ ገጥሟቸዋል፡፡ እንዲህ አይነት ቃጠሎ ደግሞ በመተንፈሻ አካላቸውም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡

ልጆቹ ወደ ሆስፒታል ከመጡ ሶስት ሳምንት ሆኗቸዋል ያሉት ዶክተር አስፈራው፤ ሲመጡ ኢንፌክሽን ፈጥሮና በሽታን የመከላከል አቅማቸው ተዳክሞ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ከመጡ በኋላ የቁስል እጥበት በማካሄድና ክትትል በማድረግ ህይወታቸውን ማትረፍ ቢቻልም አሁንም ቢሆን በልጆቹ ቀጣይ ህይወት ላይ የተደቀነ አደጋ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

እንዲህ አይነት ቃጠሎ በተለይ በመተጣጠፊያ አካል አካባቢ ጉዳት በመድረሱ የመታጠፊያ አካላቸውን ያለመታዘዝ እና በረጅም ጊዜ ደግሞ የአካል መዛባት ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል የተሻለ ህክምና ያስፈልጋቸዋል ይላሉ፡፡ በመሆኑም ከዚህ የተሻለ ህክምና የሚያገኙበት ሁኔታ ቢኖር ለልጆቹ የወደፊት እጣ ፈንታ መልካም ይሆናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት በአፋር ህዝብ ላይ ዳግም ትንኮሳ የፈጸመ ሲሆን ይህንንም ጀግኖቹ የአፋር የጸጥታ ሃይሎች ትህነግ በጀመረውን ትንኮሳ ተከትሎ በቂ ቅጣት እየተቀጣ ነው ማለታቸውን ትናንት መዘገባችን ይጣወሳል።
በወርቁ ማሩ (አፋር – አብአላ)(ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version